ዘፀአት 12:3-9 NASV

3 ለመላው የእስራኤል ሕዝብ ይህንን ንገሩ፤ ይህ ወር በገባ በአሥረኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ ጠቦት ለቤተ ሰቡ፣ አንዳንድ ጠቦት ለአባቱ ቤት ያዘጋጅ።

4 ማንኛውም ቤተ ሰብ ለአንድ ሙሉ ጠቦት ቍጥሩ አነስተኛ ከሆነ፣ በጐረቤት ያሉትን ሰዎች ቍጥር እስከ ቅርብ ከሆነው ጋር መካፈል ይኖርበታል፤ እያንዳንዱ ሰው በሚበላው መጠንም ምን ያህል ጠቦት እንደሚያስፈልግ መወሰን ይኖርባችኋል።

5 የምትመርጡት ጠቦት በግ ወይም ፍየል ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ምንም ነውር የሌለበትና አንድ ዓመት የሞላው ተባዕት መሆን አለበት።

6 ወሩ በገባ እስከ አሥራ አራተኛው ቀን ድረስ ጠብቋቸው። በዚያ ምሽት ጀምበር ስትጠልቅ የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ይረዷቸው።

7 ከዚያም ከደሙ ወስደው የጠቦቶቹ ሥጋ የሚበላበትን የእያንዳንዱን ቤት ደጃፍ መቃንና ጉበን ይቀቡ።

8 ሥጋውንም በዚያችው ሌሊት በእሳት ላይ ጠብሰው ከመራራ ቅጠልና ካልቦካ ቂጣ ጋር ይብሉት።

9 ጥሬውን ሥጋ ወይም ቅቅሉን አትብሉ፤ ነገር ግን ጭንቅላቱን፣ እግሮቹንና ሆድ ዕቃውን በእሳት ላይ ጠብሳችሁ ብሉት።