ዘፀአት 16:14-20 NASV

14 ጤዛው ከረገፈ በኋላ በሜዳው ላይ ስስ የሆነ አመዳይ የሚመስል የተጋገረ ነገር በምድረ በዳው ላይ ታየ።

15 እስራኤላውያንም ይህን ባዩ ጊዜ ምን እንደሆነ ባለማወቃቸው እርስ በርሳቸው፣ “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ተባባሉ።ሙሴም፦ “ይህ ትበሉት ዘንድ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሰጣችሁ እንጀራ ነው አላቸው።

16 እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ይሰብስብ፤ በድንኳናችሁ ባለው ሰው ልክ ለእያንዳንዱ አንድ ጐሞር ውሰዱ’ ” ብሎ እግዚአብሔር (ያህዌ) አዞአል።

17 እስራኤላውያንም እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ አንዳንዶች አብዝተው፣ አንዳንዶች ደግሞ አሳንሰው ሰበሰቡ።

18 የሰበሰቡትን በጐሞር በሰፈሩ ጊዜ ብዙ የሰበሰበው አልተረፈውም ጥቂት የሰበሰበውም አልጐደለበትም እያንዳንዱ የሰበሰበው የሚያስፈልገውን ያህል ሆነ።

19 ሙሴም፣ “ማንም ከዚህ ለነገ ምንም ማስተረፍ የለበትም” አላቸው።

20 ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ሙሴ የተናገረውን ቸል በማለት ከሰበሰቡት ውስጥ ከፊሉን አስተርፈው አሳደሩ፤ በማግሥቱም ጠዋት ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ ስለዚህ ሙሴ ተቈጣቸው።