ዘፀአት 16:20-26 NASV

20 ሆኖም ግን አንዳንዶቹ ሙሴ የተናገረውን ቸል በማለት ከሰበሰቡት ውስጥ ከፊሉን አስተርፈው አሳደሩ፤ በማግሥቱም ጠዋት ተልቶ መሽተት ጀመረ፤ ስለዚህ ሙሴ ተቈጣቸው።

21 በየማለዳው እያንዳንዱ የሚያስፈልገውን ያህል ሰበሰበ፤ ፀሓዩ እየበረታ በሄደም ጊዜ ቀለጠ።

22 ስድስተኛው ቀን ለእያንዳንዱ ሰው ሁለት ሁለት ጎሞር አድርገው እጥፍ ሰበሰቡ፤ የማኅበሩም አለቆች ወደ ሙሴ መጥተው ይህንኑ ነገሩት።

23 እርሱም አላቸው፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘው ይህ ነው፤ ‘ነገ እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ የተቀደሰ ሰንበት በመሆን፣ የዕረፍት ቀን ይሆናል። ስለዚህ መጋገር የምትፈልጉትን ጋግሩ፤ መቀቀል የምትፈልጉትን ቀቅሉ። የተረፈውን አስቀምጡ፤ እስከ ጧትም ድረስ አቆዩት።

24 ስለዚህ ሙሴ እንዳዘዘው እስከ ጧት ድረስ አቆዩት፤ አልሸተተም፤ ወይም አልተላም።

25 ሙሴም እንዲህ አለ፤ “ዛሬውኑ ብሉት፤ ዛሬ የእግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበት ነውና። ዛሬ በመሬት ላይ ምንም አታገኙም።

26 ስድስት ቀን ትሰበስቡታላችሁ፤ በሰባተኛው ቀን በሰንበት ዕለት ግን ምንም ነገር አይኖርም።”