28 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤ ትእዛዞቼንና መመሪያዎቼን ለመፈጸም እስከ መቼ እምቢ ትላላችሁ?
29 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰንበትን የሰጣችሁ መሆኑን ልብ በሉ፤ በስድስተኛው ቀን ለሁለት ቀን የሚሆን እንጀራ የሰጣችሁ ለዚህ ነው። በሰባተኛው ቀን እያንዳንዱ ሰው ባለበት ይቆይ፤ ማንም አይወጣም።”
30 ስለዚህ ሕዝቡም በሰባተኛው ቀን ዐረፉ።
31 የእስራኤልም ሕዝብ ምግቡን መና አሉት፤ እርሱም እንደ ድንብላል ዘር ነጭ፣ ጣሙም ከማር እንደ ተጋገረ ቂጣ ነበር።
32 ሙሴም አለ፤ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘን ይህ ነው፤ ‘ከግብፅ ባወጣኋችሁ ጊዜ በምድረ በዳ እንድትበሉ የሰጠኋችሁን እንጀራ ያዩ ዘንድ አንድ ጐሞር መና ወስደህ ለሚመጡት ትውልዶች አቆየው።’ ”
33 ስለዚህ ሙሴ አሮንን፣ “አንድ ማሰሮ ወስደህ አንድ ጎሞር መና አስቀምጥበት፤ ለሚመጡት ትውልዶች እንዲቆይም እግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት አስቀምጠው” አለው።
34 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው አሮን፣ መናው ይጠበቅ ዘንድ በምስክሩ ፊት አስቀመጠው።