3 ሙሴ፣ “በባዕድ አገር መጻተኛ ነኝ” ለማለት የመጀመሪያ ልጁን ስም ጌርሳም አለው።
4 “የአባቴ አምላክ ረዳቴ ነው፤ ከፈርዖን ሰይፍ አድኖኛልና” ለማለት ደግሞ ሁለተኛውን ልጁን አልዓዛር አለው።
5 የሙሴ አማት ዮቶር ከሙሴ ወንድ ልጆችና ሚስት ጋር ሆኖ በምድረ በዳ ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ተራራ አጠገብ ወደ ሰፈረበት ወደ ሙሴ መጣ።
6 ዮቶር፣ “እኔ አማትህ ዮቶር፣ ከሚስትህና ከሁለት ወንዶች ልጆቿ ጋር እየመጣን ነው” ሲል መልእክት ላከበት።
7 ስለዚህ ሙሴ አማቱን ሊቀበለው ወጣ፤ ዝቅ ብሎ እጅ በመንሣትም ሳመው፤ ከዚያም ሰላምታ ተለዋውጠው ወደ ድንኳኑ ገቡ።
8 ሙሴም እግዚአብሔር (ያህዌ) ለእስራኤል ሲል በፈርዖንና በግብፃውያን ላይ ያደረገውን ሁሉ፣ በመንገድም ላይ ስላጋጠማቸው መከራ ሁሉና እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዴት እንዳዳናቸው ለአማቱ ነገረው።
9 ዮቶርም እግዚአብሔር (ያህዌ) እነርሱን ከግብፃውያን እጅ በመታደግ ለእስራኤል ያደረገውን በጎ ነገር ሁሉ በመስማቱ ተደሰተ።