ዘፀአት 19:17-23 NASV

17 ከዚያም ሙሴ ከእግዚአብሔር (ያህዌ) ጋር ለማገናኘት ሕዝቡን ከሰፈር ይዞ ወጣ፤ ከተራራውም ግርጌ ቆሙ።

18 የሲና ተራራ እግዚአብሔር (ያህዌ) በእሳት ስለወረደበት በጢስ ተሸፍኖ ነበር። ጢሱ ከምድጃ እንደሚወጣ ጢስ ወደ ላይ ተትጐለጐለ፤ ተራራውም በሙሉ በኀይል ተናወጠ።

19 የመለከቱም ድምፅ እያየለ መጣ። ከዚያም ሙሴ ተናገረ፤ እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) በድምፅ መለሰለት።

20 እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ ጫፍ ላይ ወረደ፤ ሙሴን ወደ ተራራው ጫፍ ጠራው፤ ሙሴም ወጣ።

21 እግዚአብሔርም (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ሕዝቡ እግዚአብሔርን (ያህዌ) ለማየት በመጣደፍ ብዙዎቹ እንዳይጠፉ ውረድና አስጠንቅቃቸው

22 ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርቡት ካህናት እንኳ ራሳቸውን መቀደስ አለባቸው፤ አለዚያ እግዚአብሔር (ያህዌ) ቍጣውን ያወርድባቸዋል።”

23 ሙሴ እግዚአብሔርን (ያህዌ) እንዲህ አለው፤ “ሕዝቡ ወደ ሲና ተራራ ሊወጡ አይችሉም፤ ምክንያቱም አንተ ራስህ ‘በተራራው ዙሪያ ወሰን አድርግ፤ የተቀደሰም በማድረግ ለየው’ በማለት አስጠንቅቀኸናልና።”