ዘፀአት 19:2-8 NASV

2 ከራፊዲም ከተነሡ በኋላ ወደ ሲና ምድረ በዳ ገቡ፤ እስራኤልም በዚያ በምድረ በዳው በተራራው ፊት ለፊት ሰፈሩ።

3 ከዚያም ሙሴ ወደ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወጣ፤ እግዚአብሔርም (ያህዌ) ከተራራው ጠራውና እንዲህ አለው፤ “ለያዕቆብ ቤት የምትለው ለእስራኤልም ሕዝብ የምትናገረው ይህ ነው፤

4 ‘በግብፅ ላይ ያደረግሁትን፣ በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል።

5 አሁንም በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣

6 እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤’ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃሎች እነዚህ ናቸው።”

7 ስለዚህ ሙሴ ተመልሶ የሕዝቡን አለቆች አስጠራ፤ እንዲናገር እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ቃሎች ሁሉ ነገራቸው።

8 ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ላይ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ፤ ስለዚህ ሙሴ እነርሱ ያሉትን መልሶ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወሰደ።