7 ከሐሰት ክስ ራቅ፤ በደል የሌለበትን ወይም ትክክለኛውን ሰው ለሞት አሳልፈህ አትስጥ፣ በደለኛውን ንጹሕ አላደርግምና።
8 “ጒቦ አትቀበል፤ ጒቦ፣ አጥርተው የሚያዩትን ሰዎች ዐይን ያሳውራል፤ የጻድቃንንም ቃል ያጣምማልና።
9 “መጻተኛውን አትጨቁን፤ በግብፅ መጻተኛ ስለ ነበራችሁ፣ መጻተኛ ምን እንደሚሰማው እናንተ ራሳችሁ ታውቃላችሁና።
10 “ስድስት ዓመት በእርሻህ ላይ ዝራ፤ አዝመራንም ሰብስብ፤
11 ነገር ግን በሰባተኛው ዓመት ምድሪቱን ሳትጠቀምባትና ሳታርሳት እንዲሁ ተዋት፤ ከዚያም በወገንህ መካከል ያሉት ድኾች ከእርሷ ምግብ ያገኛሉ፤ የዱር አራዊትም ከእነርሱ የተረፈውን ይበላሉ። በወይን ቦታህና በወይራ ዛፎችህም ላይ እንዲሁ አድርግ።
12 “ስድስት ቀን ሥራህን ሥራ፤ በሬህና አህያህ በቤትህ የተወለደው ባሪያና መጻተኛው ያርፉ ዘንድ በሰባተኛው ቀን ምንም አትሥራ።
13 ያልኋችሁን ሁሉ ታደርጉ ዘንድ ተጠንቀቁ፤ የሌሎችን አማልክት ስም አትጥሩ፤ ከአፋችሁም አይስሙ።