1 “ከፍታው ሦስት ክንድ የሆነ መሠዊያ ከግራር ዕንጨት ሥራ፤ ርዝመቱ አምስት፣ ስፋቱም አምስት ክንድ ሆኖ ባለ አራት ማእዘን ይሁን።
2 ቀንዶቹና መሠዊያው አንድ ወጥ ይሆኑ ዘንድ በአራቱም ማእዘኖች ላይ ቀንድ አድርግለት፤ መሠዊያውንም በነሐስ ለብጠው።
3 ዕቃዎቹን ሁሉ ይኸውም የዐመድ ማስወገጃ ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን፣ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፣ ሜንጦዎችንና የፍም መያዣዎችን ከነሐስ አብጃቸው።
4 ዐመድ ማውረጃ የሚሆን እንደ መረብ የሆነ የነሐስ ፍርግርግ አድርግለት በአራቱም የመረብ ማእዘኖች ላይ የነሐስ ቀለበቶች አብጅ።
5 እስከ መሠዊያው ወገብ እንዲደርስ በመሠዊያው ዙሪያ ባለው እርከን ሥር አድርገው።
6 የግራር ዕንጨት መሎጊያዎችን ለመሠዊያው ሠርተህ በነሐስ ለብጣቸው።
7 በሸክም ጊዜ በመሠዊያው ሁለቱም ጎኖች እንዲሆኑ፣ መሎጊያዎቹ በቀለበቶቹ ውስጥ ይግቡ።