ዘፀአት 3:15-21 NASV

15 ደግሞም እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሙሴን፣ “የአባቶቻችሁ የአብርሃም አምላክ፣ የይስሐቅ አምላክ፣ የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ወደ እናንተ ልኮኛል፤ ስሜም ለዘለዓለም ይኸው ነው፤ ወደ ፊት በተከታታይ በሚነሣው ትውልድ ሁሉ የምታሰበው በዚህ ስም ነው ብለህ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው” አለው።

16 “ሂድና የእስራኤልን አለቆች ሰብስበህ፣ የአባቶቻችሁ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠልኝና እንዲህ አለኝ፤ ጐብኝቻችኋለሁ፤ በግብፅ የደረሰባችሁንም አይቻለሁ።

17 ስለዚህም በግብፅ ከምትቀበሉት መከራ አውጥቼ ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር አገባችኋለሁ ብሎአል ብለህ ንገራቸው” አለኝ።

18 “የእስራኤል አለቆችም ይሰሙሃል። አንተና የእስራኤል አለቆች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትሄዱና፣ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠልን፤ ስለዚህም ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ ተጒዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንድናቀርብ ፍቀድልን’ ብላችሁ ትነግሩታላችሁ።

19 የግብፅ ንጉሥ ግን በኀያል ክንድ ካልተገደደ በስተቀር መቼም እንደማይለቃችሁ አውቃለሁ።

20 ስለዚህ እኔ እጅግ ድንቅ የሆኑ ታምራትን እዚያው እመካከላቸው በማድረግ ክንዴን ዘርግቼ ግብፃውያንን እመታቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትሄዱ ይለቃችኋል።

21 ይህ ሕዝብ በግብፃውያን ዘንድ የመወደድን ጸጋ እንዲያገኝ ስለማደርግ በምትወጡበት ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም።