ዘፀአት 3:17-22 NASV

17 ስለዚህም በግብፅ ከምትቀበሉት መከራ አውጥቼ ማርና ወተት ወደምታፈሰው ወደ ከነዓናውያን፣ ወደ ኬጢያውያን፣ ወደ አሞራውያን፣ ወደ ፌርዛውያን፣ ወደ ኤዊያውያንና ኢያቡሳውያን ምድር አገባችኋለሁ ብሎአል ብለህ ንገራቸው” አለኝ።

18 “የእስራኤል አለቆችም ይሰሙሃል። አንተና የእስራኤል አለቆች ወደ ግብፅ ንጉሥ ትሄዱና፣ ‘የዕብራውያን አምላክ እግዚአብሔር (ያህዌ) ተገለጠልን፤ ስለዚህም ወደ ምድረ በዳ የሦስት ቀን መንገድ ተጒዘን ለአምላካችን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት እንድናቀርብ ፍቀድልን’ ብላችሁ ትነግሩታላችሁ።

19 የግብፅ ንጉሥ ግን በኀያል ክንድ ካልተገደደ በስተቀር መቼም እንደማይለቃችሁ አውቃለሁ።

20 ስለዚህ እኔ እጅግ ድንቅ የሆኑ ታምራትን እዚያው እመካከላቸው በማድረግ ክንዴን ዘርግቼ ግብፃውያንን እመታቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እንድትሄዱ ይለቃችኋል።

21 ይህ ሕዝብ በግብፃውያን ዘንድ የመወደድን ጸጋ እንዲያገኝ ስለማደርግ በምትወጡበት ጊዜ ባዶ እጃችሁን አትሄዱም።

22 እያንዳንዷ ዕብራዊት ከጎረቤቷም ይሁን አብራት ከምትኖረው ግብፃዊት የብርና የወርቅ ጌጣጌጦች እንደዚሁም ልብስ እንድ ትሰጣት ትጠይቅ። እነዚህንም ሁሉ ወስዳችሁ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁን ታስጌጧቸዋላችሁ፤ ታለብሷቸዋላችሁም። በዚህም መንገድ የግብፃውያኑን ሀብት በእጃችሁ አግብታችሁ ትወጣላችሁ።”