4 ለመሠዊያውም ከጠርዝ በታች ሆኖ ከመሠዊያው ግማሽ ቁመት ላይ የሚሆን የናስ ፍርግርግ ማንደጃ ሠሩ።
5 ለናሱ ፍርፍርግ ማንደጃ አራት ማእዘኖች መሎጊያዎቹን እንዲይዙ የናስ ቀለበቶችን ሠሩ።
6 መሎጊያዎቹን ከግራር ዕንጨት ሠርተው በናስ ለበጧቸው።
7 መሠዊያውን ለመሸከም በመሠዊያው ጐኖች ይሆኑ ዘንድ መሎጊያዎቹን በቀለበቶቹ ውስጥ አስገቧቸው፤ ውስጡንም ክፍት በማድረግ ከሳንቃዎች ሠሩት።
8 የናስ መታጠቢያ ሳሕንና የናስ መቆሚያውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ ከሚያገለግሉት ሴቶች መስተዋት ሠሩት።
9 ቀጥሎም አደባባዩን ሠሩ፤ የደቡቡ ክፍል ርዝመት አንድ መቶ ክንድ ሲሆን፣ በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ የተሠሩ መጋረጃዎች ነበሩት፤
10 ሃያ ምሰሶዎችና ሃያ የናስ መቆሚያዎች፣ የብር ኵላቦችና በምሰሶዎቹ ላይ ዘንጎች ነበሩት።