19 ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ከኤፉዱ ቀጥሎ ካሉት ከሌሎቹ ሁለት የደረት ኪስ ጐኖች ጋር ከውስጠኛው ጠርዝ ላይ አያያዟቸው።
20 ከዚያም ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተው ልክ ከኤፉዱ መታጠቂያ በላይ፣ ከመጋጠሚያው አጠገብ፣ ከኤፉዱ ፊት ለፊት ካሉት ከትከሻ ንጣዮች ጋር አያያዟቸው።
21 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን እንዳዘዘው የደረት ኪሱ ከኤፉዱ ተነጥሎ ለብቻው እንዳይንጠለጠል የደረት ኪሱን ቀለበቶች ከመታጠቂያው ጋር በማገናኘት፣ ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ፈትል አሠሯቸው።
22 የኤፉዱን ቀሚስ በሸማኔ ሥራ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ጨርቅ ሠሩት፤
23 ይህም እንደ ክሳዱ ቅድ ከቀሚሱ መካከል ላይ አንገትጌ ነበረው፤ እንዳይተረተርም በአንገትጌው ዙሪያ ላይ ቅምቅማት ነበረው።
24 በቀሚሱ ጠርዝ ዙሪያ ከሰማያዊ፣ ከሐምራዊና ከቀይ ማግ እንዲሁም በቀጭኑ ከተፈተለ በፍታ ላይ ሮማኖቹን አደረጉ።
25 ከንጹሕ ወርቅም ሻኵራዎችን ሠሩ፤ እነዚህንም በሮማኖቹ መካከል በጠርዙ ዙሪያ አደረጉ።