ዘፀአት 6:3-9 NASV

3 ሁሉን የሚችል አምላክ (ኤሎሂም) ሆኜ ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ ተገለጥሁላቸው፤ ነገር ግን እግዚአብሔር (ያህዌ) በተባለው ስሜ ራሴን አልገለጥሁላቸውም።

4 በእንግድነት የሚኖሩባትን የከነዓንን ምድር እንድሰጣቸው ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን ገብቻለሁ።

5 ደግሞም በግብፃውያን ሥር በባርነት ሆነው ያሰሙትን የእስራኤላውያንን የሥቃይ ድምፄ ሰምቻለሁ ኪዳኔንም አስታውሻለሁ።

6 “ስለዚህ ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ ‘እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ፤ ከግብፃውያን ቀንበር አወጣችኋለሁ። ለእነርሱ ባሪያ ከመሆን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድና በታላቅ ፍርድ እቤዣችኋለሁ።

7 “የራሴ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላክ (ኤሎሂም) እሆናችኋለሁ ከግብፃውያን ቀንበር ያላቀቅኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላክ (ያህዌ ኤሎሂም) መሆኔንም ታውቃላችሁ።

8 ከዚያም ለአብርሃም፣ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብ እሰጣችኋለሁ ብዬ ወደማልሁላቸው ምድር አመጣችኋለሁ፤ ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ። እኔ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነኝ።’ ”

9 ሙሴ ይህን ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ ተስፋ ከመቍረጣቸውና ከአስከፊ እስራታቸው የተነሣ ግን አላዳመጡትም።