18 ስለዚህ ነገ በዚህ ጊዜ ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ በግብፅ ላይ ወርዶ የማያውቅ አስከፊ የበረዶ ማዕበል እልካለሁ።
19 ከብቶችህና በመስክ ላይ ያለህ ማንኛውም ነገር ወደ መጠለያ ይገቡ ዘንድ አሁን ትእዛዝ ስጥ፤ ምክንያቱም በረዶው ወደ መጠለያ ባልገቡትና በመስክ ላይ በቀሩት በማንኛውም ሰውና እንስሳት ላይ ወርዶባቸው ስለሚሞቱ ነው።
20 የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል የፈሩት የፈርዖን ሹማምቶች፣ ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን ለማስገባት ተጣደፉ።
21 የእግዚአብሔርን (ያህዌ) ቃል ችላ ያሉት ግን ባሮቻቸውንና ከብቶቻቸውን በመስክ ላይ እንደ ነበሩ ተዉአቸው።
22 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን፣ “በመላይቱ የግብፅ ምድር ባሉት ሰዎች፣ በእንስሳት እንዲሁም በምድሪቱ ላይ በሚበቅሉት ነገሮች ሁሉ ላይ በረዶ እንዲወርድ እጅህን ወደ ሰማይ አንሣ” አለው።
23 ሙሴ በትሩን ወደ ሰማይ ባነሣ ጊዜ እግዚአብሔር (ያህዌ) ነጐድጓድና በረዶ አወረደ፤ መብረቅም በምድሪቱ ላይ ሆነ። እግዚአብሔር (ያህዌ) በግብፅ ምድር በረዶ አዘነበ፤
24 በረዶ ወረደ፤ መብረቅም አብረቀረቀ፤ ግብፅ ሐገር ከሆነችበት ዘመን አንሥቶ በምድሪቱ ሁሉ እንደዚህ ያለ አስከፊ ማዕበል ሆኖ አያውቅም።