25 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የዱር እንስሳትን እንደየወገናቸው፣ ከብቶችን እንደየወገናቸው፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚሳቡ ፍጡራንን እንደየወገናቸው አደረገ። እግዚአብሔርም (ኤሎሂም) ይህ መልካም እንደሆነ አየ።
26 እግዚአብሔር (ኤሎሂም)፣ “ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር በሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው” አለ።
27 ስለዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤በእግዚአብሔር (ኤሎሂም) መልክ ፈጠረው፤ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።
28 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “ብዙ ተባዙ፤ ምድርን ሙሏት፤ ግዟትም፤ የባሕርን ዓሦች፣ የሰማይን ወፎች፣ እንዲሁም በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትን ሕያዋን ፍጡራንን ሁሉ ግዟቸው” ብሎ ባረካቸው።
29 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ እንዲህ አለ፤ “በምድር ላይ ያሉትን ዘር የሚሰጡ ተክሎችን ሁሉ፣ በፍሬያቸው ውስጥ ዘር ያለባቸውን ዛፎች ሁሉ ምግብ ይሆኑላችሁ ዘንድ ሰጥቻችኋለሁ።
30 እንዲሁም ለምድር አራዊት ሁሉ፣ ለሰማይ ወፎች ሁሉ፣ በምድር ላይ ለሚንቀሳቀሱ ሕያዋን ፍጡራን ሁሉ ማንኛውም ለምለም ተክል ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቻለሁ” እንዳለውም ሆነ።