ዘፍጥረት 16:4-10 NASV

4 አብራምም ከአጋር ጋር ተኛ፤ እርሷም ፀነሰች። አጋርም ነፍሰ ጡር መሆኗን ባወቀች ጊዜ እመቤቷን መናቅ ጀመረች።

5 ሦራም አብራምን፣ “ለደረሰብኝ በደል ተጠያቂው አንተ ነህ፤ አገልጋዬ ዕቅፍህ ውስጥ እንድትገባ እኔው ሰጠሁህ፤ አሁን ግን ይኸው ማርገዟን ስታውቅ ትንቀኝ ጀመር፤ እግዚአብሔር (ያህዌ) በአንተና በእኔ መካከል ይፍረድ” አለችው።

6 አብራምም፣ “አገልጋይሽ እንደሆነች በእጅሽ ውስጥ ናት፤ የፈለግሽውን አድርጊባት” አላት። ከዚያም ሦራ ስላሠቃየቻት አጋር ጥላት ኰበለለች።

7 የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ አጋርን በአንድ የውሃ ምንጭ አጠገብ በምድረ በዳ አገኛት፤ ምንጩም ወደ ሱር በሚወስደው መንገድ ዳር ነበር።

8 መልአኩም፣ “የሦራ አገልጋይ አጋር ሆይ፤ ከየት መጣሽ? ወዴትስ ትሄጃለሽ?” አላት፤እርሷም፣ “ከእመቤቴ ከሦራ ኰብልዬ መምጣቴ ነው” ብላ መለሰች።

9 የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ፣ “ወደ እመቤትሽ ተመለሽ፤ ለእርሷም ተገዥላት” አላት።

10 ደግሞም መልአኩ፣ “ዘርሽን እጅግ አበዛለሁ፤ ከብዛቱም የተነሣ ሊቈጠር አይችልም” አላት።