ዘፍጥረት 22:1-7 NASV

1 ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን ፈተነው፤ “አብርሃም!” አለው። እርሱም “አቤቱ አለሁ” አለ።

2 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “የምትወደውን አንዱን ልጅህን፣ ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው።

3 በማግስቱ ጠዋት አብርሃም ማልዶ ተነሣ፤ አህያውን ጭኖ፣ ሁለት አገልጋዮቹንና ልጁን ይስሐቅን ይዞ፣ ለመሥዋዕት የሚበቃውን ዕንጨት ከቈረጠ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጒዞውን ጀመረ፤

4 በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ፤

5 አገልጋዮቹንም “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቈዩን፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ሰግደን እንመለሳለን” አላቸው።

6 አብርሃም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን ዕንጨት ወስዶ፣ ልጁን ይስሐቅን አሸከመው፤ እሳቱንና ቢላዋውንም ራሱ ያዘ። ሁለቱም አብረው ሄዱ።

7 ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን፣ “አባቴ ሆይ” አለው።አብርሃምም፣ “እነሆኝ፤ አለሁ ልጄ” አለው።ይስሐቅም፣ “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት የት አለ?” ብሎ ጠየቀ።