4 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ለአብርሃም ሰጥቶ የነበረውን አንተም በስደት የምትኖርበትን ይህችን ምድር ርስት አድርጎ ያወርስህ ዘንድ፣ ለአብርሃም የሰጠውን በረከት ለአንተና ለዘርህ ይስጥ።
5 ይስሐቅም ያዕቆብን በሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ ወደሚኖረው፣ የያዕቆብና የዔሳው እናት የርብቃ ወንድም ወደ ሆነው ወደ ሶርያዊው የባቱኤል ልጅ ወደ ላባ ላከው።
6 ዔሳው፣ ይስሐቅ ያዕቆብን መርቆ ሚስት እንዲያገባ ወደ ሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ እንደ ላከውና በባረከውም ጊዜ ከነዓናዊት ሴት እንዳያገባ ትእዛዝ እንደ ሰጠው ሰማ።
7 ያዕቆብ የአባት የእናቱን ፈቃድ ለመፈጸም፣ ወደ መስጴጦምያ መሄዱንም ተረዳ።
8 በዚህም የከነዓናውያን ሴቶች በአባቱ በይስሐቅ ዘንድ የቱን ያህል የተጠሉ መሆናቸውን ተገነዘበ፤
9 ስለዚህም ወደ እስማኤል ሄደ፣ የአብርሃም ልጅ እስማኤል የወለዳትን፣ የነባዮትን እኅት ማዕሌትን በሚስቶቹ ላይ ተጨማሪ አድርጎ አገባ።
10 ያዕቆብ ከቤርሳቤህ ተነሥቶ ወደ ካራን ሄደ።