ዘፍጥረት 38:24-30 NASV

24 ከሦስት ወር ያህል በኋላ፣ “ምራትህ ትዕማር ዘማዊ ሆናለች፤ ከዚህም የተነሣ አርግዛለች” ተብሎ ለይሁዳ ተነገረው።ይሁዳም፣ “አውጧትና በእሳት ተቃጥላ ትሙት” አለ።

25 እርሷም ተይዛ በምትወሰድበት ጊዜ ለዐማትዋ፣ “እኔ ያረገዝሁት የእነዚህ ዕቃዎች ባለቤት ከሆነ ሰው ነው” ስትል ላከችበት፤ ደግሞም፣ “የማኅተሙ ቀለበት ከነማንጠልጠያውና በትሩ የማን እንደሆነ እስቲ ተመልከት” አለችው።

26 ይሁዳም ዕቃዎቹን ዐውቆ፣ “ልጄ ሴሎም እንዲያገባት ባለማድረጌ፣ እርሷ ከእኔ ይልቅ ትክክል ናት” አለ። ከዚያም በኋላ ከእርሷ ጋር አልተኛም።

27 የመውለጃዋ ጊዜ እንደ ደረሰም ፅንሷ መንታ መሆኑ ታወቀ።

28 በምትወልድበትም ጊዜ አንደኛው እጁን አወጣ፤ አዋላጂቱም፣ “ይህኛው መጀመሪያ ወጣ” ስትል በእጁ ላይ ቀይ ክር አሰረችለት፤

29 ነገር ግን፣ እጁን መልሶ ሲያስገባ ወንድሙ ተወለደ። አዋላጂቱም “አንተ እንዴት ጥሰህ ወጣህ!” አለች፤ ከዚያም ስሙ ፋሬስ ተባለ።

30 ከዚያ በኋላ እጁ ላይ ቀይ ክር የታሰረለት ወንድሙ ተወለደ፣ ስሙም ዛራ ተባለ።