ዘፍጥረት 42:15-21 NASV

15 ታናሽ ወንድማችሁ እዚህ እስካልመጣ ድረስ ከዚህ ንቅንቅ እንደማትሉ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ማንነታችሁ የሚረጋገጠውም በዚህ ነው።

16 በሉ፣ ከእናንተ አንዱን ላኩና ወንድማችሁን ይዞ ይመለስ፤ የቀራችሁት ግን የተናገራችሁት ቃል እስኪረጋገጥ ድረስ፣ እስር ቤት ትቈያላችሁ። እንደ ተናገራችሁት ካልሆነ ግን፣ በፈርዖን ስም እምላለሁ፤ ሁላችሁም ሰላዮች ናችሁ” አላቸው።

17 ሁሉንም ሦስት ቀን በእስር አቈያቸው።

18 በሦስተኛውም ቀን ዮሴፍ እንዲህ አላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) ስለምፈራ እንዲህ በማድረግ ሕይወታችሁን አትርፉ።

19 ታማኝ ሰዎች ከሆናችሁ፣ ከመካከላችሁ አንዱ እዚህ እስር ቤት ሲቈይ፣ የቀራችሁት ግን ለተራቡት ቤተ ሰቦቻችሁ እህል ትወስዱላቸዋላችሁ፤

20 ታናሽ ወንድማችሁን ግን ይዛችሁ መምጣት አለባችሁ፤ በዚህም የተናገራችሁት ቃል እውነተኛነት ይረጋገጣል፤ እናንተም ከመሞት ትተርፋላችሁ።” እነርሱም ይህንኑ ለመፈጸም ተስማሙ።

21 እርስ በርሳቸውም፣ “ይኸው በወንድማችን ላይ ባደረስነው በደል ምክንያት ቅጣታችንን እየተቀበልን ነው። እርሱ እንደዚያ ተጨንቆ ስለ ሕይወቱ ሲማጠነን፣ እኛ አልሰማነውም ነበር፤ ይህ መከራ የደረሰብንም በዚሁ ምክንያት ነው” ተባባሉ።