ዘፍጥረት 42:22-28 NASV

22 ሮቤልም መልሶ፣ “በዚህ ልጅ ላይ፣ ‘ክፉ ነገር አታድርጉ’ ብዬ አልነበረምን? እናንተ ግን አልሰማችሁኝም፤ ስለዚህም ደሙ ከእጃችን ይፈለጋል” አላቸው።

23 ዮሴፍ የሚያነጋግራቸው በአስተርጓሚ ስለ ሆነ የሚነጋገሩትን እንደሚሰማቸው አላወቁም ነበር።

24 ከፊታቸውም ዘወር ብሎ አለቀሰ፤ ከዚያም ወደ እነርሱ ተመልሶ እንደ ገና አነጋገራቸው፤ ስምዖንንም ከእነርሱ ለይቶ ዐይናቸው እያየ አሰረው።

25 በስልቻዎቻቸው እህል እንዲሞሉላቸው፤ ብሩንም በያንዳንዱ ሰው ስልቻ ውስጥ መልሰው እንዲያስቀምጡና ለጒዞአቸው ስንቅ እንዲያሲዟቸው ዮሴፍ ትእዛዝ ሰጠ። ይህም ከተደረገላቸው በኋላ፣

26 እህላቸውን በአህዮቻቸው ጭነው ጒዞአቸውን ቀጠሉ።

27 በመንገድም ለዐዳር ሰፍረው ሳሉ፣ ከእነርሱ አንዱ ከያዘው እህል ላይ ለአህያው ለመስጠት ስልቻውን ሲፈታ፣ በስልቻው አፍ ላይ ብሩን አገኘ።

28 እርሱም ወንድሞቹን፣ “ኧረ ብሬ ተመልሶልኛል፤ ይኸው ስልቻዬ ውስጥ አገኘሁት” አላቸው።ሁሉም ልባቸው በድንጋጤ ተሞልቶ እየተንቀጠቀጡ በመተያየት፣ “እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ምን ሊያመጣብን ይሆን?” አሉ።