ዘፍጥረት 48:7-13 NASV

7 ከሰሜን ምዕራብ መስጴጦምያ መልስ ኤፍራታ ለመድረስ ጥቂት ሲቀረኝ፣ እናትህ ራሔል በከነዓን ምድር ሞታብኝ ዐዘንሁ። እኔም ወደ ኤፍራታ ማለት ወደ ቤተ ልሔም በሚወስደው መንገድ ዳር ቀበርኋት።”

8 እስራኤልም የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ፣“እነዚህ እነማን ናቸው?” ሲል ጠየቀ፤

9 ዮሴፍም፣ “እነዚህ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) የሰጠኝ ልጆች ናቸው” ብሎ ለአባቱ መለሰለት፤ እስራኤልም፣ “አቅርባቸውና ልመርቃቸው” አለ።

10 በዚህ ጊዜ እስራኤል ዐይኖቹ በእርጅና ምክንያት በመድከማቸው አጥርቶ ማየት ይሳነው ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን አባቱ ዘንድ አቀረባቸው፤ አባቱም ስሞ ዐቀፋቸው።

11 እስራኤልም ዮሴፍን፣ “ዐይንህን እንደ ገና ዐያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ግን ልጆችህን ጭምር ለማየት አበቃኝ” አለው።

12 ዮሴፍም ልጆቹን ከእስራኤል ጒልበት ፈቀቅ በማድረግ አጐንብሶ በግንባሩ መሬት ላይ ተደፋ።

13 ከዚያም ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ይዞ ኤፍሬምን ከራሱ በስተ ቀኝ፣ ከእስራኤል በስተ ግራ፣ ምናሴን ደግሞ ከራሱ በስተ ግራ፣ ከእስራኤል በስተ ቀኝ በኩል አቀረባቸው።