ዘፍጥረት 6:3-9 NASV

3 እግዚአብሔርም (ያህዌ)፣ “ሰው ሟች ስለ ሆነ መንፈሴ እያዘነ ከእርሱ ጋር ለዘላለም አይኖርም፤ ዕድሜው 120 ዓመት ይሆናል” አለ።

4 የእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ልጆች የሰዎችን ሴቶች ልጆች ተገናኝተው ልጆች በወለዱ ጊዜም ሆነ ከዚያም በኋላ ኔፊሊም የተባሉ ሰዎች በምድር ላይ ነበሩ። እነርሱም በጥንቱ ዘመን በጀግንነታቸው ከፍ ያለ ዝና ያተረፉ ናቸው።

5 እግዚአብሔር (ያህዌ) አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ።

6 እግዚአብሔር (ያህዌ) ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፤ ልቡም እጅግ አዘነ።

7 ስለዚህም እግዚአብሔር (ያህዌ)፣ “የፈጠርሁትን የሰው ዘር ከምድረ ገጽ አጠፋለሁ፤ ከሰው እስከ እንስሳ በምድር ላይ ከሚሳቡ ፍጡራን እስከ ሰማይ ወፎች አጠፋለሁ፤ ስለ ፈጠርኋቸው ተጸጽቻለሁና” አለ።

8 ኖኅ ግን በእግዚአብሔር (ያህዌ) ዘንድ ሞገስን አገኘ።

9 የኖኅ ታሪክ እንደሚከተለው ነው፤ ኖኅ በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ጻድቅና ከበደል የራቀ ሰው ነበር፤ አካሄዱንም ከእግዚአብሔር (ኤሎሂም) ጋር አደረገ።