ሐዋርያት ሥራ 3:11-17 NASV

11 የተፈወሰውም ለማኝ ከጴጥሮስና ዮሐንስ ጋር ጥብቅ ብሎ አብሮአቸው ሳለ፣ ሕዝቡ ሁሉ በመገረም እነርሱ ወደነበሩበት ‘የሰሎሞን መመላለሻ’ ወደተባለው ስፍራ እየሮጡ መጡ።

12 ጴጥሮስም ይህን ባየ ጊዜ እንዲህ አላቸው፤ “የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ በዚህ ለምን ትደነቃላችሁ? ደግሞም በእኛ ኀይል ወይም በእኛ ጽድቅ ይህ ሰው ድኖ እንዲመላለስ እንዳደረግነው በመቊጠር፣ ለምን ወደ እኛ አትኵራችሁ ትመለከታላችሁ?

13 የአባቶቻችን አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ ብላቴናውን ኢየሱስን አከበረው፤ እናንተ ግን እንዲሞት አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ጲላጦስ ሊፈታው ቢፈልግም እናንተ በእርሱ ፊት ካዳችሁት፤

14 ቅዱሱንና ጻድቁን ክዳችሁ ነፍሰ ገዳዩ እንዲፈታላችሁ ለመናችሁ፤

15 የሕይወት መገኛ የሆነውን ገደላችሁት፤ እግዚአብሔር ግን ከሙታን አስነሣው፤ እኛም ለዚህ ምስክሮች ነን።

16 ይህ የምታዩትና የምታውቁት ሰው የበረታው በኢየሱስ ስም በማመን ነው፤ ሁላችሁም እንደምታዩት ፍጹም ፈውስ እንዲያገኝ ያደረገው የኢየሱስ ስምና በእርሱ አማካይነት የሚገኘው እምነት ነው።

17 “አሁንም ወንድሞች ሆይ፤ እናንተ ይህን ያደረጋችሁት እንደ አለቆቻችሁ ሁሉ ባለማወቅ እንደሆነ ዐውቃለሁ።