4 ቀጥሎም ዙፋኖችን አየሁ፤ በዙፋኖቹም ላይ ለመፍረድ ሥልጣን የተሰጣቸው ሰዎች ተቀምጠው ነበር፤ ደግሞም ስለ ኢየሱስ ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል የተሰየፉትን ሰዎች ነፍሶች አየሁ። እነርሱ ለአውሬው ወይም ለእርሱ ምስል አልሰገዱም፤ በግምባራቸው ወይም በእጃቸው ላይ የአውሬውን ምልክት አልተቀበሉም፤ እነርሱም ከሞት ተነሥተው ከክርስቶስ ጋር ሺህ ዓመት ነገሡ።
5 የቀሩት ሙታን ግን ሺሁ ዓመት እስኪፈጸም ድረስ ከሞት አልተነሡም። ይህ የመጀመሪያው ትንሣኤ ነው።
6 በመጀመሪያው ትንሣኤ ተካፋይ የሚሆኑ ብፁዓንና ቅዱሳን ናቸው። ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፤ ከእርሱም ጋር ሺህ ዓመት ይነግሣሉ።
7 ሺሁም ዓመት ሲፈጸም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል፤
8 በአራቱ የምድር ማእዘናት ያሉትን ሕዝቦች፦ ጎግንና ማጎግን እያሳተ ለጦርነት ሊያሰልፋቸው ይወጣል፤ ቍጥራቸው በባሕር ዳርቻ እንዳለ አሸዋ ነው።
9 እነርሱም ወደ ምድር ሁሉ ወጥተው የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ ከበቡ፤ ነገር ግን እሳት ከሰማይ ወርዶ በላቸው።
10 ያሳታቸው ዲያብሎስም፣ አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ ወዳሉበት ወደ እሳቱና ወደ ዲኑ ባሕር ተጣለ፤ እነርሱም ቀንና ሌሊት ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሠቃያሉ።