ራእይ 4:1-7 NASV

1 ከዚህ በኋላ እነሆ በሰማይ የተከፈተ በር አየሁ፤ ቀደም ሲል እንደ መለከት ሲናገረኝ የሰማሁት ድምፅ፣ “ወደዚህ ና፤ ከዚህም በኋላ ሊሆን የሚገባውን ነገር አሳይሃለሁ” አለ

2 እኔም ወዲያወኑ በመንፈስ ነበርሁ፤ እነሆም፤ በሰማይ ዙፋን ቆሞአል፤ በዙፋኑም ላይ የተቀመጠ ነበረ።

3 ተቀምጦም የነበረው የኢያስጲድንና የሰርዲኖን ዕንቊ ይመስል ነበር። የመረግድ ዕንቊ የመሰለ ቀስተ ደመናም ዙፋኑን ከቦት ነበር።

4 በዙፋኑ ዙሪያ ሌሎች ሃያ አራት ዙፋኖች ነበሩ፤ በእነርሱም ላይ ነጭ ልብስ የለበሱና በራሳቸውም ላይ የወርቅ አክሊል የደፉ ሃያ አራት ሽማግሌዎች ተቀምጠው ነበር።

5 ከዙፋኑም መብረቅና ድምፅ፣ ነጐድጓድም ወጣ፤ በዙፋኑ ፊት ሰባት መብራቶች ይበሩ ነበር፤ እነዚህም ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት ናቸው።

6 ደግሞም በዙፋኑ ፊት እንደ መስተዋት የጠራ የብርጭቆ ባሕር ነበረ።በዙፋኑ መካከል፣ በዙሪያውም ከፊትና ከኋላ በዐይን የተሞሉ አራት ሕያዋን ፍጡራን ነበሩ።

7 የመጀመሪያው ሕያው ፍጡር አንበሳ፣ ሁለተኛው በሬ ይመስሉ ነበር፤ ሦስተኛው የሰው ፊት የሚመስል ፊት ነበረው፤ አራተኛው ደግሞ የሚበር ንስር ይመስል ነበር።