18 በእነዚያ ቅርንጫፎች ላይ አትኵራራ። ብትኰራ ግን ይህን አስተውል፤ አንተ ሥሩን አትሸከምም፤ ሥሩ ግን አንተን ይሸከምሃል እንጂ።
19 እንግዲህ፣ “ቅርንጫፎች የተሰበሩት እኔ እንድገባ ነው” ትል ይሆናል።
20 ትክክል ነው፤ እነርሱ የተሰበሩት ካለማመን የተነሣ ነው፤ አንተም በእምነት ቆመሃል፤ ፍራ እንጂ ትዕቢተኛ አትሁን።
21 እግዚአብሔር በተፈጥሮ ቅርንጫፎች ለሆኑት ካልራራላቸው፣ ለአንተም አይራራልህምና።
22 እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ጭካኔ ተመልከት፤ ጭካኔውም በወደቁት ላይ ነው፤ ቸርነቱ ግን በቸርነቱ ውስጥ እስካለህ ድረስ ለአንተ ነው፤ ያለዚያ ግን አንተም ትቈረጣለህ።
23 እነርሱም ባለማመናቸው ጸንተው ባይኖሩ፣ ተመልሰው ይገባሉ፤ እግዚአብሔር መልሶ ሊያስገባቸው ይችላልና።
24 የበረሓ ከሆነው የወይራ ዛፍ የተቈረጥህና ተፈጥሮህ ወዳልሆነው ወደ መልካሙ ወይራ የገባህ ከሆንህ፣ በተፈጥሮአቸው ቅርንጫፎቹ የሆኑት እነዚህ ወደ ራሳቸው ወይራ ዛፍ መግባታቸውማ ምን ያህል ይሆን?