1 በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ የዳን ነገድም በእስራኤል ነገዶች መካከል ርስተ ድርሻውን ገና ስላልወሰደ፣ የሚሰፍርበትን የራሱን ርስት ይፈልግ ነበር።
2 ስለዚህ ዳናውያን ምድሪቱን እንዲሰልሉና እንዲመረምሩ አምስት ኀያላን ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ከተሞች ወደዚያ ላኩ፤ እነዚህም ነገዶቻቸውን ሁሉ የሚወክሉ ነበሩ። የላኳቸውም ሰዎች፣ “ሂዱ፤ ምድሪቱን ሰልሉ” አሏቸው።መልእክተኞቹም ወደ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር ገቡ፤ ወደሚያድሩበትም ወደ ሚካ ቤት መጡ።
3 በሚካ ቤት አጠገብ እንደ ደረሱም የወጣቱን ሌዋዊ ድምፅ ዐወቁ፤ ስለዚህ ወደዚያ ጐራ ብለው፣ “ወደዚህ ያመጣህ ማን ነው? እዚህ ምን ትሠራለህ? የመጣኸውስ ለምንድን ነው?”። ሲሉ ጠየቁት።
4 እርሱም፣ “ሚካ ይህን ይህን አደረገልኝ ቀጠረኝ፤ ካህኑም ሆንሁ” አላቸው።
5 እነርሱም፣ “መንገዳችን መቃናት አለመቃናቱን እንድናውቅ እባክህ እግዚአብሔርን ጠይቅልን” አሉት።
6 ካህኑም፣ “በሰላም ሂዱ፤ መንገዳችሁን እግዚአብሔር አቃንቶላችኋል” ብሎ መለሰላቸው።