1 ናዖድ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን እንደ ገና በእግዚአብሔር ፊት ከፉ ድርጊት ፈጸሙ።
2 ስለዚህም እግዚአብሔር በሐጾር ሆኖ ይገዛ ለነበረው ለከነዓን ንጉሥ ለኢያቢስ አሳልፎ ሸጣቸው። የኢያቢስ ሰራዊት አዛዥ፣ በሐሮሼትሐጎይም የሚኖረው ሲሣራ ነበረ፤
3 እርሱም ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎች ስለ ነበሩት እስራኤላውያንን ሃያ ዓመት እጅግ አስጨነቃቸው፤ እነርሱም ይረዳቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ።
4 በዚያን ጊዜ የለፊዶት ሚስት ነቢዪቱ ዲቦራ በእስራኤል ላይ ፈራጅ ነበረች።
5 እርሷም በኰረብታማው በኤፍሬም ምድር፣ በራማና በቤቴል መካከል ካለው የዲቦራ ዘንባባ ዛፍ ሥር ተቀምጣ ትፈርድ ነበር፤ እስራኤላውያንም ለፍርድ ወደ እርሷ ይመጡ ነበር።
6 ዲቦራ፣ በንፍታሌም ውስጥ ቃዴስ በተባለች ከተማ ይኖር የነበረውን የአቢኒኤምን ልጅ ባራቅን አስጠርታ እንዲህ አለችው፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ያዝሃል፤ “ተነሣ፤ ከንፍታሌምና ከዛብሎን ዐሥር ሺህ ሰዎች ይዘህ ወደ ታቦር ተራራ ውጣ፤
7 እኔም የኢያቢስን ሰራዊት አዛዥ ሲሣራን ከሠረገሎቹና ከሰራዊቱ ጋር ቂሶን ወንዝ እንዲመጣ አነሣሣዋለሁ፤ በእጅህም አሳልፌ እሰጥሃለሁ።”
8 ባርቅም፣ “አብረሽኝ የምትሄጂ ከሆነ እሄዳለሁ፤ አብረሽኝ የማትሄጂ ከሆነ ግን አልሄድም” አላት።
9 ዲቦራ መልሳ፣ “ይሁን እሺ፤ መሄዱን አብሬህ እሄዳለሁ፤ በዚህ ሁኔታ የምትሄድ ከሆነ ግን ክብሩ ለአንተ አይሆንም፤ እግዚአብሔር ሲሣራን ለሴት አሳልፎ ይሰጣልና” አለችው። ስለዚህ ዲቦራ ከባርቅ ጋር ወደ ቃዴስ ሄደች፤
10 በዚያም ባርቅ ለዛብሎንና ለንፍታሌም ሰዎች ጥሪ አስተላለፈ፤ ዐሥር ሺህ ሰዎች ተከተሉት፤ ዲቦራም አብራው ሄደች።
11 በዚያን ጊዜ ቄናዊው ሔቤር፣ የሙሴ ዐማች የአባብ ልጆች ከሆኑት ከሌሎቹ ቄናውያን ተለይቶ በቃዴስ አጠገብ ጻዕናይም ከተባለ ቦታ ከሚገኘው ትልቅ ወርካ ጥግ ድንኳኑን ተክሎ ነበር።
12 የአቢኒዔም ልጅ ባርቅ ወደ ታቦር ተራራ መሄዱን ሲሣራ በሰማ ጊዜ፣
13 ዘጠኝ መቶ የብረት ሠረገሎችንና ከአሪሶት ሐጎይም እስከ ቂሶን ወንዝ ያለውን ሰራዊቱን በሙሉ አሰባሰበ።
14 በዚህ ጊዜ ዲቦራ ባርቅን፣ “ተነሣ! እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሰጠባት ቀን ይህች ናት፤ እነሆ እግዚአብሔር በፊትህ ቀድሞ ወጥቶአል” አለቸው። ስለዚህ ባርቅ ዐሥር ሺህ ሰዎችን አስከትሎ ከታቦር ተራራ ወረደ።
15 እግዚአብሔር ሲሣራንና ሠረገሎቹን ሁሉ በባርቅ ፊት በሰይፍ ስለት እጅግ ተሸንፈው ወደ ኋላ እንዲያፈገፍጉ አደረገ፤ ሲሣራም ከሠረገላው ወርዶ በእግሩ ሸሸ፤
16 ባርቅ ግን የሲሣራን ሠረገሎችና ሰራዊቱን እስከ አሪሶት ሐጎይም ድረስ አሳደዳቸው፤ የሲሣራ ሰራዊት በሙሉ በሰይፍ ወደቀ፤ በሕይወት የተረፈ አንድም ሰው አልነበረም።
17 በሐጾር ንጉሥ በኢያቡስና በቄናዊው በሔቤር ጐሣ መካከል መልካም ግንኙነት ስለ ነበር ሲሣራ በእግሩ ሸሽቶ የቄናዊው የሔቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ኢያዔል ድንኳን ሮጠ።
18 ኢያዔልም ወጥታ ሲሣራን ተቀበለችውና፣ “ጌታዬ፤ ወደ ውስጥ ግባ፤ ፈጽሞ አትፍራ” አለችው፤ ሲሣራም ወደ ድንኳኗ ገባ፤ እርሷም በልብስ ሸፍና ደበቀችው።
19 ሲሣራም፣ “ጠምቶኛልና እባክሽን ውሃ አጠጪኝ” አላት፤ እርሷም የወተት ጮጮውን ከፍታ የሚጠጣውን ሰጠችው፤ እንደ ገናም ሸፈነችው።
20 እርሱም፣ “በድንኳኑ በር ላይ ቁሚ፤ ማንም ሰው መጥቶ፣ “እዚህ ሰው አለ?” ቢልሽ፣ “የለም በይ” አላት።
21 የሔቤር ሚስት ኢያዔል ግን ሲሣራ ደክሞ፣ ከባድ እንቅልፍም ወስዶት ሳለ፣ የድንኳን ካስማና መዶሻ ይዛ በቀስታ ወደ እርሱ ቀረበች፤ ከዚያም ካስማውን በመዶሻ ጆሮ ግንዱ ላይ መትታ ከመሬት ጋር ሰፋችው፤ እርሱም ሞተ።
22 ባርቅ ሲሣራን በመከታተል ላይ ስለ ነበር ከዚያ ሲደርስ፣ ኢያዔል ከድንኳኗ ወጥታ “ና፤ የምትፈልገውን ሰው አሳይሃለሁ” አለችው፤ ስለዚህ ከእርሷ ጋር ወደ ድንኳንዋ ገባ፤ ሲሣራም በጆሮ ግንዱ ላይ ካስማ እንደ ተመታበት ሞቶ ተዘርሮ ነበረ።
23 በዚያች ዕለት እግዚአብሔር የከነዓንን ንጉሥ ኢያቢስን በእስራኤላውያን ፊት እንዲሸነፍ አደረገው፤
24 ከነዓናዊውን ንጉሥ ኢያቢስን እስኪደመስሱ ድረስ የእስራኤላውያን ክንድ እየበረታ ሄደ።