መሳፍንት

ምዕራፎች 14

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

የሳምሶን ጋብቻ

1ሳምሶን ወደ ተምና ወረደ፤ እዚያም አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አየ። 2እንደተመለሰም አባቱንና እናቱን፣ “በተምና አንዲት ወጣት ፍልስጥኤማዊት አይቻለሁና አሁኑኑ አጋቡኝ” አላቸው። 3አባቱና እናቱም፣ “ከዘመዶችህ ወይም ከሕዝባችን ሁሉ መካከል ለአንተ የምትሆን ሴት መች ታጣችና ነው ወዳልተገረዙት ፍልስጥኤማውያን ሚስት ፍለጋ የሄድኸው?” አሉት።ሳምሶንም አባቱን፣ “ልቤን የማረከችው እርሷ ናትና እርሷን አጋባኝ” አለው። 4በዚያን ጊዜ በእስራኤል ላይ ገዦቹ ፍልስጥኤማውያን ስለ ነበሩ፣ ከፍልስጥኤማውያን ጋር ጠብ እንዲፈጠር እግዚአብሔር ሆን ብሎ ያደረገው ነገር መሆኑን አባቱና እናቱ አላወቁም ነበር። 5ከዚያም ሳምሶን ከአባቱና ከእናንቱ ጋር ወደ ተምና ወረደ፤ በዚያም ከአንድ የወይን አትክልት ቦታ እንደ ደረሱ፣ ድንገት አንድ የአንበሳ ደቦል እያገሣ መጣበት። 6በዚህ ጊዜ የእግዚአብሔር መንፈስ በኀይል ወረደበት፤ ስለዚህ የፍየል ጠቦት እንደሚገነጣጠል አንበሳውን ያለ ምንም መሣሪያ በባዶ እጁ ገነጣጠለው፤ ያደረገውን ግን ለአባቱም ሆነ ለእናቱ አልነገራቸውም ነበር። 7ወደ ሴቲቱም ወረደ፤ ከእርሷም ጋር ተነጋገረ፤ እጅግም ወደዳት። 8ከጥቂት ቀን በኋላም ሊያገባት ተመለሰ፤ የአንበሳውንም በድን ለማየት ከመንገድ ዘወር አለ፤ በበድኑም ውስጥ የንብ መንጋ ሰፍሮ ተመለከተ፤ ማርም ነበረበት፤ 9በእጁ ወስዶም መንገድ ለመንገድ እየበላ ሄደ፤ ከወላጆቹም ጋር እንደተገናኘም ከማሩ ሰጣቸው፤ እነርሱም በሉ። ነገር ግን ማሩን የወሰደው ከአንበሳ በድን መሆኑን አልነገራቸውም ነበር። 10የሳምሶን አባት ልጅቱን ሊያይ ወረደ፤ ሳምሶንም በነበረው የሙሽራ ወግ መሠረት በዚያ ግብዣ አደረገ። 11እርሱም ለፍልስጥኤማውያን በታየ ጊዜ፣ ሠላሳ አጃቢዎች ሰጡት። 12ሳምሶን እንዲህ አላቸው፤ አንድ እንቈቅልሽ እነግራችኋለሁ፤ ታዲያ ፍቺውን በሰርጉ በዓል ሰባት ቀኖች ውስጥ ከሰጣችሁኝ፣ ሠላሳ የቀጭን ፈትል በፍታ ቀሚስና ሠላሳ የክት ልብስ እሰጣችኋለሁ። 13እንቈቅልሹን ካልፈታችሁልኝ ግን ሠላሳ የቀጭን ፈትል በፍታ ቀሚስና ሠላሳውን የክት ልብስ እናንተ ትሰጡኛላችሁ።”እነርሱም፣ “በል እንቈቅልሽህን ንገረንና እንስማው” አሉት። 14ሳምሶንም፣“ከበላተኛው መብል፣ከብርቱም ጣፋጭ ነገር ወጣ” አላቸው።እነርሱም እስከ ሦስት ቀን ድረስ እንቈቅልሹን መፍታት አልቻሉም ነበር። 15በአራተኛው ቀን የሳምሶንን ሚስት፣ “የእንቈቅልሹን ፍች እንዲነግረን ባልሽን እስቲ አግባቢልን፤ ያለዚያ አንቺንም የአባትሽንም ቤተ ሰብ በእሳት እናቃጥላችኋለን፤ ጠርታችሁ የጋበዛችሁን ልትዘርፉን ነው?” አሏት። 16ከዚያ የሳምሶን ሚስት ተንሰቅስቃ እያለቀሰች ከፊቱ በመቅረብ፣ “ለካስ ትጠላኛለህ! በእርግጥ አትወደኝም” አለችው።እርሱም፣ “ይህን ለአባቴም ሆነ ለእናቴ አልነገርኋቸውም፤ ታዲያ ለአንቺ ለምን እነግርሻለሁ?” አላት። 17ሚስቱም በሰርጉ በዓል ሰባት ቀን ሙሉ እያለቀሰች ጨቀጨቀችው፤ አጥብቃ ስለ ነዘነዘችውም በመጨረሻ በሰባተኛው ቀን ነገራት፤ እርሷም በበኩሏ የእንቈቅልሹን ፍች ለሕዝቧ ነገረች። 18በሰባተኛው ቀን ፀሓይ ከመጥለቋ በፊት የከተማው ሰዎች፣“ከማር የጣፈጠ ምን ተገኝቶ?ከአንበሳስ ወዲያ ብርቱ ከየት መጥቶ!” አሉት።ሳምሶንም መልሶ፣“በጊደሬ ባላረሳችሁ፣እንቈቅልሼንም ባልፈታችሁ” አላቸው። 19ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በሳምሶን ላይ በኀይል ወረደበት፤ ወደ አስቀሎናም ወርዶ ከሰዎቻቸው መካከል ሠላሳውን ገደለ፤ ያላቸውንም ከገፈፈ በኋላ ልብሶቻቸውን አምጥቶ እንቈቅልሹን ለፈቱት ሰዎች ሰጣቸው። በቍጣ እንደነደደም ተነሥቶ ወደ አባቱ ቤት ወጣ። 20የሳምሶንም ሚስት ለሚዜው ተዳረች።