መሳፍንት
ምዕራፎች 3
መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም
1በዚህ ጊዜ በከነዓን ላይ በተደረጉት ጦርነቶች ተሳትፈው የማያውቁትን እስራኤላውያን ለመፈተን፣ እግዚአብሔር ባሉበት የተዋቸው ሕዝቦች እነዚህ ናቸው፤
2ይህን ማድረጉ ቀደም ሲል በጦር ሜዳ ውለው የማያውቁትን የእስራኤል ልጆች የጦርነት ልምድ እንዲያገኙ ለማድረግ ብቻ ነው፤
3እነዚህም አሕዛብ አምስቱ የፍልስጥኤም ገዦች፣ ከነዓናውያን በሙሉ፣ ሲዶናውያንና ከበኣል አርሞንዔም ተራራ እስከ ሐማት መግቢያ ባሉት የሊባኖስ ተራሮች የሚኖሩ ኤዊያውያን ነበሩ።
4እነዚህ፣ እግዚአብሔር በሙሴ በኵል ለቀደሙ አባቶቻቸው የሰጠውን ትእዛዛት ማክበር አለማክበራቸውን ለማወቅ መፈተኛ እንዲሆኑ እዚያው የቀሩ ነበሩ።
5ስለዚህ እስራኤላውያን ከከነዓናውያን፣ ከኬጢያውያን፣ ከአሞራውያን፣ ከፌርዛውያን፣ ከኤዊያውያንና ከኢያቡሳውያን ጋር አብረው ኖሩ።
6እስራኤላውያን የእነዚህን ሴቶች ልጆች አገቡ፤ የራሳቸውንም ሴቶች ልጆች ለእነርሱ ወንዶች ልጆች ዳሩ፤ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ።