መሳፍንት 21 NASV

ለብንያማውያን ሚስት ስለ ማግኘት

1 እስራኤላውያን በምጽጳ፣ “ከእኛ አንድም ሰው ሴት ልጁን በጋብቻ ለብንያማውያን መዳር የለበትም” በማለት ተማምለው ነበር።

2 ሕዝቡ ወደ ቤቴል ሄደው በዚያም እስከ ማታ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ተቀመጡ፤ ድምፃቸውንም ከፍ በማድረግ አምርረው አለቀሱ፤

3 እንዲህም አሉ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይህ ለምን በእስራኤል ላይ ሆነ? ዛሬ ከእስራኤል አንድ ነገድ እንዴት ይታጣ?”

4 በማግሥቱ ጠዋት ሕዝቡ መሠዊያ ሠሩ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትና የኅብረት መሥዋዕት አቀረቡ።

5 በምጽጳ፣ በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ያልተገኘ ማንኛውም ሰው መገደል አለበት ብለው እስራኤላውያን ተማምለው ስለ ነበር፣ “ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ሳይወጣ የቀረ ማን አለ?” ሲሉ ጠየቁ።

6 በዚህ ጊዜ እስራኤላውያን ስለ ወንድሞቻቸው ስለ ብንያማውያን በማዘን እንዲህ አሉ፤ “ዛሬ ከእስራኤል ነገዶች አንዱ ታጥቷል፤

7 ሴቶች ልጆቻችንን ለእነዚህ ብንያማውያን በጋብቻ ላንሰጥ በእግዚአብሔር ስለ ማልን ለተረፉት እንዴት ሚስት ልናገኝላቸው እንችላለን?”

8 ከዚያም፣ “ከእስራኤል ነገዶች ምጽጳ ላይ በእግዚአብሔር ጉባኤ ፊት ሳይወጣ የቀረ ማን ነው” ሲሉ ጠየቁ፤ ታዲያ ከኢያቢስ ገለዓድ አንድም ሰው ለጉባኤው ወደ ሰፈሩ አለመምጣቱን ተረዱ፤

9 ሕዝቡን ሲቈጥሩም ከኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች አንድም ሰው አልነበረምና።

10 ስለዚህ ዐሥራ ሁለት ሺህ ተዋጊዎች ወደ ኢያቢስ ገለዓድ ሄደው በእዚያ የሚኖሩትን በሙሉ ሴቶቹንና ሕፃናቱን ጭምር በሰይፍ እንዲፈጇቸው ጉባኤው መመሪያ ሰጥቶ ላካቸው።

11 እነርሱም፣ “እንግዲህ የምታደርጉት ይህ ነው፤ ወንዱን በሙሉ እንዲሁም ድንግል ያልሆኑትን ሴቶች ሁሉ ግደሉ” አሏቸው።

12 በኢያቢስ ገለዓድ ከሚኖረው ሕዝብ መካከል ወንድ ያልደረ ሰባቸው አራት መቶ ደናግል አገኙ፤ በከነዓን ምድር በሴሎ ወደ ሚገኘውም ሰፈር አመጧቸው።

13 ከዚያም ጉባኤው በሙሉ በሬሞን ዐለት ወዳሉት ብንያማውያን የሰላም ጥሪ አስተላለፈ።

14 ስለዚህ በዚህን ጊዜ ብንያማውያን ተመለሱ፤ ከመገደል የተረፉትንም የኢያቢስ ገለዓድ ሴቶች ሰጧቸው፤ ይሁን እንጂ የሴቶቹ ቊጥር ለሁሉም የሚበቃ አልነበረም።

15 እግዚአብሔር በእስራኤል ነገዶች መካከል አስደንጋጭ ስብራት ስላደረገ የእግዚአብሔር ሕዝብ ለብንያማውያን አዘነ።

16 የጉባኤውም መሪዎች እንዲህ አሉ፤ “እነሆ፤ የብንያም ሴቶች አልቀዋል፤ ታዲያ ለቀሩት ወንዶች ሚስት የምናገኝላቸው እንዴት ነው?

17 ከእስራኤል ነገዶች አንዱ የሆነው እንዳይጠፋ አሁን በሕይወት ያሉት ብንያማውያን ወራሽ የሚሆን ዘር ሊኖራቸው ይገባል።

18 ‘ልጁን ለብንያማዊ የሚድር ርጉም ይሁን’ ብለን እኛ እስራኤላውያን ስለ ተማማልን እንግዲህ ልጆቻችንን ልንድርላቸው አንችልም፤

19 ይሁን እንጂ ከቤቴል በስተ ሰሜንና ከቤቴል ወደ ሴኬም በሚወስደው መንገድ በስተ ምሥራቅ እንዲሁም ከለቦና በስተ ደቡብ ባለችው በሴሎ የእግዚአብሔር በዓል በየዓመቱ ይከበራል።”

20 ስለዚህም ለብንያማውያን እንዲህ ሲሉ መመሪያ ሰጧቸው፤ “ሄዳችሁ በወይኑ የአትክልት ስፍራ ተደበቁ፤

21 አድፍጣችሁ ተጠባበቁ። የሴሎ ልጃገረዶች ለጭፈራ ወደዚያ በሚወጡበት ጊዜ፣ ከወይኑ አትክልት ቦታ ወጥታችሁ ከልጃገረዶቹ ለየራሳችሁ ሚስት ጥለፉ፤ ወደ ብንያምም ምድር ሂዱ።

22 አባቶቻቸውም ሆኑ ወንድሞቻቸው ቢቃወሙ፣ ‘በጦርነት ጊዜ ለእያንዳንዳቸው የሚሆኑ ሚስቶች ስላላገኘን ነውና እነርሱን በመርዳት ምሕረት አድርጉልን፤ እናንተም ደግሞ ልጆቻችሁን ፈቅዳችሁ ያልዳራችሁ በመሆናችሁ በደለኞች አትሆኑም’ እንላቸዋለን።”

23 ብንያማውያን እንደ ተባሉት አደረጉ፤ ልጃገረዶቹ በሚጨፍሩበትም ጊዜ እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ እየጠለፈ ሚስት እንድትሆነው ይዞ ሄደ፤ ከዚያም ወደ ርስታቸው ተመለሱ፤ ከተሞቻቸውንም አድሰው በዚያ ኖሩ።

24 በዚያን ጊዜ እስራኤላውያን ያን ቦታ ትተው ወደየቤታቸው፣ ወደየርስታቸው፣ ወደየጐሣቸውና ወደየነገዳቸው ሄዱ።

25 በዚያን ዘመን በእስራኤል ንጉሥ አልነበረም፤ እያንዳንዱም ሰው መልካም መስሎ የታየውን ያደርግ ነበር።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21