መሳፍንት

ምዕራፎች 6

መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም

ጌዴዎን

1እንደ ገና እስራኤላውያን በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸሙ፤ እግዚአብሔርም ለምድያማውያን አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱም ሰባት ዓመት ገዟቸው። 2እስራኤላውያን የምድያማውያን ኀይል ስለ በረታባቸው በየዋሻውና በየምሽጉ፣ በየተራራው ጥግ መሸሸጊያ ስፍራ አበጁ። 3እስራኤላውያን ዘር በሚዘሩበት ጊዜ ሁሉ ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች መጥተው አገሩን ይወሩ ነበር። 4እነርሱም በምድሪቱ ላይ ሰፍረው እስከ ጋዛ ያለውን ሰብል በማጥፋት አንዳችም የእህል ዘር አያስተርፉም፣ የበግም ሆነ የከብት ወይም የአህያ መንጋ አይተዉም ነበር። 5ከብቶቻቸውንና ድንኳኖቻቸውን ይዘው ሲመጡ ልክ የአንበጣ መንጋ ይመስሉ ነበር፤ ሰዎቹንም ሆነ ግመሎቻቸውን ለመቍጠር አዳጋች ሲሆን፣ የሚመጡትም ምድሪቱን ለማጥፋት ነበር። 6ምድያማውያን እስራኤላውያንን ችግር ላይ ስለጣሏቸው፣ ይረዳቸው ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። 7ከምድያማውያን ጥቃት የተነሣ እስራኤላውያን ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፤ 8እግዚአብሔር አንድ ነቢይ ላከላቸው፤ እርሱም እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከባርነት ቤት ከግብፅ ምድር ያወጣኋችሁ እኔ ነኝ። 9ከግብፃውያን እጅ ታደግኋችሁ፤ ከሚያስ ጨንቋችሁ ሁሉ አዳንኋችሁ፤ እነርሱንም ከፊታችሁ አሳድጄ አስወጣኋቸው፤ ምድራቸውንም ሰጠኋችሁ። 10እናንተንም፣ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ በምድራቸው ላይ የምትኖሩባቸው የአሞራውያንን አማልክት አታምልኩ አልኋችሁ፤ እናንተ ግን አላዳመጣችሁኝም።” 11 የእግዚአብሔር መልአክ ዖፍራ ወደምትባል መንደር መጥቶ፣ በአቢዔዝራዊው በኢዮአስ ዕርሻ ውስጥ በሚገኝ በአንድ የባሉጥ ዛፍ ሥር ተቀመጠ፤ የኢዮአስም ልጅ ጌዴዎን፣ ምድያማውያን እንዳያዩበት ደብቆ በወይን መጭመቂያው ስፍራ ስንዴውን ይወቃ ነበር። 12የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦ፣ “አንተ ኀያል ጦረኛ እነሆ፤ እግዚአብሔር ከአንተ ጋር ነው” አለው። 13ጌዴዎን መልሶ፣ “ጌታዬ ሆይ፤ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ ይህ ሁሉ እንዴት ሊደርስብን ቻለ? ‘እግዚአብሔር ከግብፅ ምድር አውጥቶናል’ በማለት አባቶቻችን የነገሩን ታምራት የት አለ? አሁን ግን እግዚአብሔር ትቶናል፤ በምድያማውያንም እጅ አሳልፎ ሰጥቶናል” አለው። 14በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ዘወር ብሎ፣ ‘ሂድ፤ ባለህ ኀይል እስራኤላውያንን ከምድያማውያን እጅ ነጻ እንድ ታወጣ የምልክህ እኔ አይደለሁምን? አለው”። 15ጌዴዎንም፣ “ጌታ ሆይ፤ የእኔ ጐሣ ከምናሴ ነገድ እጅግ ደካማ ነው፤ ከቤተሰቤም እኔ የመጨረሻ ነኝ፤ ታዲያ እንዴት እኔ እስራኤልን ላድን እችላለሁ?” አለ። 16 እግዚአብሔርም፣ “በእርግጥ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ ምድያማውያንንም እንደ አንድ ሰው አድርገህ ትመታቸዋለህ” አለው። 17ጌዴዎን እንዲህ ብሎ መለሰ፤ “አሁን በፊትህ ሞገስ አግኝቼ ከሆነ በእርግጥ የምታነጋግረኝ አንተ ራስህ ለመሆንህ ምልክት ስጠኝ፤ 18ተመልሼ እስክመጣ፣ መሥዋዕቴንም አምጥቼ በፊትህ እስካቀርብ ድረስ እባክህ አትሂድ።” እግዚአብሔርም፣ “እስክትመለስ እጠብቅሃለሁ” አለው። 19ጌዴዎን ወደ ቤቱ ሄደ፤ የፍየል ጠቦትም ዐረደ፤ አንድ ኢፍ መስፈሪያ ዱቄት ወስዶ እርሾ ያልገባበት ቂጣ ጋገረ። ሥጋውን በቅርጫት፣ መረቁን በምንቸት ይዞ በመምጣት በባሉጥ ሥር ለተቀመጠው አቀረበለት። 20 የእግዚአብሔር መልአክ፣ “ሥጋውንና ዕርሾ ያልገባበትን ቂጣ ወስደህ፣ በዚያ ዐለት ላይ አኑር፤ መረቁንም በሥጋውና በቂጣው ላይ አፍስስ” አለው፤ ጌዴዎንም እንደታዘዘው አደረገ። 21መልአኩም በያዘው በትር ጫፍ ሥጋውንና ቂጣውን ነካ፤ ከዐለቱም እሳት ወጥቶ ሥጋውንና ቂጣውን በላ፤ ከዚያም የእግዚአብሔር መልአክ ተሰወረ። 22ጌዴዎን ያየው የእግዚአብሔር መልአክ መሆኑን ባወቀ ጊዜ፣ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ፤ የእግዚአብሔርን መልአክ ፊት ለፊት አይቻለሁና ወዮልኝ” አለ። 23 እግዚአብሔርም፣ “ሰላም ለአንተ ይሁን፤ አትፍራ፤ አትሞትም” አለው። 24ጌዴዎንም በዚያ ለእግዚአብሔር መሠዊያ ሠራ፤ ስሙንም “እግዚአብሔር ሰላም ነው” ብሎ ጠራው፤ ይህ መሠዊያ የአቢዔዝራውያን ይዞታ በሆነው በዖፍራ ዛሬም ቆሞ ይታያል። 25በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር ጌዴዎንን እንዲህ አለው፤ “ከአባትህ መንጋ ሰባት ዓመት የሆነውን ሁለተኛውን ወይፈን ውሰድ፤ አባትህ ለበኣል የሠራውን መሠዊያ አፍርስ፤ በአጠገቡ የአሼራን ዐምድ ሰባብረህ ጣል። 26በዚህ ፍርስራሽ ጒብታ ላይ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር የሚገባውን መሠዊያ ሥራ። ሰባብረህ በጣልኸው የአሼራ ምስል ዐምድ ሁለተኛውን ወይፈን ወስደህ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ አቅርበው።” 27ጌዴዎን ከአገልጋዮቹ ዐሥር ሰዎች ወስዶ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ቤተ ሰቡንና የከተማውን ሰው ስለ ፈራ ይህን ያደረገው ቀን ሳይሆን ሌሊት ነበር። 28ሌሊቱ ነግቶ የከተማው ሕዝብ ከመኝታው ሲነሣ፣ የበኣል መሠዊያ ፈርሶ በአጠገቡ የቆመው የአሼራ ምስል ተሰባብሮ፣ አዲስ በተሠራው መሠዊያ ላይ ሁለተኛው ወይፈን ተሠውቶ ነበር። 29እነርሱም፣ “ይህን ያደረገ ማን ነው?” በማለት እርስ በርሳቸው ተጠያየቁ።ነገሩን በጥብቅ ሲከታተሉም፣ “የኢዮአስ ልጅ ጌዴዎን መሆኑን ደረሱበት።” 30የከተማዪቱም ሰዎች ኢዮአስን፣ “የበኣልን መሠዊያ ያፈረሰና በአጠገቡ የቆመውን የአሼራን ምስል ዐምድ የሰበረው ልጅህ በመሆኑ መሞት ስላለበት አውጣልን አሉት።” 31በዚህ ጊዜ ኢዮአስ በቍጣ ለገነፈለውና በዙሪያው ለነበረው ሕዝብ እንዲህ አለ፤ “ለበኣል ትሟገቱለታላችሁን? ልታድኑትስ ትሞክራላችሁን? ለእርሱ የሚሟገትለት ቢኖር እስከ ጠዋት ይሙት! እንግዲህ በኣል በእርግጥ አምላክ ከሆነ መሠዊያውን ሲያፈርሱበት ራሱን ሊከላከል ይችላል።” 32ስለዚህም፣ “መሠዊያውን አፍርሶበታልና ራሱ በኣል ይሟገተው” ሲሉ በዚያ ዕለት ጌዴዎንን፣ “ይሩበኣል” ብለው ጠሩት። 33በዚህ ጊዜ ምድያማውያን ሁሉ፣ አማሌቃውያንና ሌሎች የምሥራቅ ሕዝቦች ኀይላቸውን አስተባብረው የዮርዳኖስን ወንዝ በመሻገር በኢይዝራኤል ሸለቆ ሰፈሩ። 34ከዚያም የእግዚአብሔር መንፈስ በጌዴዎን ላይ ወረደ፤ እርሱም መለከት ነፋ፤ አቢዔዝራውያን እንዲከተሉት ጠራቸው። 35እንዲሁም በመላው የምናሴ ምድር መልእክተኞቹን ልኮ እንዲከተሉት ጥሪ አደረገ፤ ደግሞም የአሴር፣ የዛብሎንና የንፍታሌም ሰዎች ወጥተው እንዲገጥሟቸው መልእክተኛ ላከባቸው። 36ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “በተናገርኸው መሠረት እስራኤላውያንን በእጄ የምታድናቸው ከሆነ፣ 37እነሆ፤ የበግ ጠጒር ባዘቶ በዐውድማው ላይ አኖራለሁ። ምድሩ በሙሉ ደረቅ ሆኖ ባዝቶው ላይ ብቻ ጤዛ ቢኖር፣ እንዳልኸው እስራኤላውያንን በእኔ እጅ እንደምታድናቸው ዐውቃለሁ።” 38እንደዚሁ ሆነ፤ ጌዴዎን በማግስቱ ጠዋት ማልዶ ተነሣ፤ ባዘቶውንም ሲጨምቅ የወጣው ውሃ አንድ ቈሬ ሞላ። 39ከዚያም ጌዴዎን እግዚአብሔርን እንዲህ አለው፤ “እባክህ አትቈጣኝ፤ አንዲት ጥያቄ እንደ ገና ልጠይቅ። በጠጒሩ ባዘቶ ላይ ሌላ ሙከራ እንዳደርግ ፍቀድልኝ፤ በዚህ ጊዜ ምድሩ ሁሉ በጤዛ ተሸፍኖ ባዘቶው ደረቅ ይሁን።” 40በዚያች ሌሊት እግዚአብሔር እንደ ተጠየቀው አደረገ፤ ምድሩ በሙሉ በጤዛ ሲሸፈን፣ ባዘቶው ብቻ ደረቅ ሆነ።