11 ከዚያ በኋላም ከዳን ወገን ለጦርነት ዝግጁ የሆኑ ስድስት መቶ ሰዎች ከጾርዓና ከኤሽታኦል ተነሡ።
12 ወጥተውም በይሁዳ ምድር ባለችው በቂርያትይዓሪም ሰፈሩ፤ እንግዲህ ከቂርያትይዓሪም በስተ ምዕራብ ያለው ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የዳን ሰፈር መባሉ ከዚሁ የተነሣ ነው።
13 ከዚያም ተጒዘው ወደ ኰረብታማው የኤፍሬም አገር በመሄድ ወደ ሚካ ቤት መጡ።
14 የላይሽን ምድር ሰልለው የነበሩት አምስቱ ሰዎች ለወንድሞቻቸው፣ “ከእነዚሁ ቤቶች በአንዱ ኤፉድ፣ ተራፊም፣ የተቀረጸ ምስልና ቀልጦ የተሠራ ጣዖት እንዳለ ታውቃላችሁን? እንግዲህ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ ዕወቁበት” አሏቸው።
15 ስለዚህ ወጣቱ ሌዋዊ ወደሚኖርበት ወደ ሚካ ቤት ጎራ ብለው ሰላምታ አቀረቡለት።
16 ለጦርነት ተዘጋጅተው የመጡት ስድስት መቶ የዳን ሰዎች በቅጥሩ በር መግቢያ ላይ ቆመው ነበር።
17 ካህኑ ለጦርነት ከተዘጋጁት ስድስት መቶ ሰዎች ጋር በቅጥሩ በር ላይ ቆሞ ሳለ፣ ምድሪቱን ለመሰለል መጥተው የነበሩትን አምስት ሰዎች ወደ ቤቱ ውስጥ በመግባት የተቀረጸውን ምስልና ኤፉዱን፣ ተራፊሙንና ቀልጦ የተሠራውን ምስል ወሰዱ።