13 ቀጥሎም፣ “በል ና፤ ወደ ጊብዓ ወይም ወደ ራማ ለመድረስ እንሞክርና ከዚያ በአንዱ ስፍራ እናድራለን” አለው።
14 ስለዚህም መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ የብንያም ነገድ ወደሆነችው ወደ ጊብዓ እንደ ደረሱም ፀሓይ ጠለቀች።
15 ለማደርም ወደዚያው ጎራ አሉ፤ ሄደውም በከተማዪቱ አደባባይ ተቀመጡ፤ ሆኖም በቤቱ ለማሳደር ማንም አልተቀበላቸውም ነበር።
16 በዚያች ምሽት ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር መጥቶ በጊብዓ የሚኖር አንድ መጻተኛ ሽማግሌ ከዕርሻ ሥራው መጣ፤ የዚያ አገር ሰዎች ግን ብንያማውያን ነበሩ።
17 ሽማግሌው ቀና ብሎ መንገደኛውን በከተማዪቱ አደባባይ ላይ ባየው ጊዜ፣ “ከወዴት መጣህ? ወዴትስ ትሄዳለህ?” ሲል ጠየቀው።
18 ሰውየውም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኛ የመጣነው ከይሁዳ ቤተ ልሔም ርቆ ከሚገኘው ከኰረብታማው ከኤፍሬም አገር ነው፤ ከይሁዳ ቤተ ልሔም ነበርሁ፤ አሁን ወደ እግዚአብሔር ቤት እሄዳለሁ፤ ወደ ቤቱ የሚወስደኝ ሰው አላገኘሁም።
19 ለአህዮቻችን ገለባና ገፈራ አለን፤ እኛ ባሮችህ ለእኔም ሆነ ለገረድህ፣ አብሮን ላለውም ወጣት እንጀራና የወይን ጠጅ ይዘናል፤ ሌላ ምንም ነገር አያስፈልገንም።”