1 ካህኑ አልዓዛር፣ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል የየነገዱ ጐሣ አባቶች የደለደሉላቸው፣ እስራኤላውያንም በከነዓን ምድር የወረሱት ርስት ይህ ነው።
2 ርስታቸውም እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት፣ ለዘጠኙ ነገድና ለእኩሌታው ነገድ በዕጣ ተከፋፈለ።
3 ሙሴ ለሁለቱ ነገድና ለእኩሌታው፣ የዮርዳኖስን ምሥራቅ ክፍል ርስት አድርጎ ሰጣቸው፤ ሌዋውያኑ ግን አብረዋቸው እንዲካፈሉ አላደረገም፤
4 የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ሆነው ነበርና፤ ለሌዋውያኑ ግን ከሚኖሩባቸው ከተሞች እንዲሁም ለበግ፣ ለፍየልና ለከብት መንጎቻቸው መሰማሪያ እንዲሆን አብሮ የተከለለላቸውን ምድር ብቻ እንጂ ሌላ አልሰጣቸውም፤
5 ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት፣ ምድሪቱን ተካፈሉ።
6 የይሁዳም ሰዎች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ከዚያም የቄኔዛዊው የዮፎኒ ልጅ ካሌብ እንዲህ አለው፤ “እግዚአብሔር በቃዴስ በርኔ ስለ አንተና ስለ እኔ፣ የአምላክ ሰው ለሆነው ለሙሴ የተናገረውን ታውቃለህ።