5 ለቀሩት ለቀዓት ዘሮች ደግሞ ከኤፍሬምና ከዳን ነገድ ጐሣዎች፣ እንዲሁም ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ጐሣዎች ዐሥር ከተሞች በዕጣ ተመደቡላቸው።
6 ለጌርሶን ዝርያዎች ከይሳኮር፣ ከአሴር፣ ከንፍታሌም ነገድ ጐሣዎችና ባሳን ውስጥ ካለው ከምናሴ ነገድ እኩሌታ ጐሣዎች ዐሥራ ሦስት ከተሞች ተመደቡላቸው።
7 ለሜራሪ ዝርያዎች በየጐሣቸው ከሮቤል፣ ከጋድና ከዛብሎን ነገዶች ዐሥር ከተሞች ተመደቡላቸው።
8 ስለዚህ እስራኤላውያን እግዚአብሔር በሙሴ በኩል ባዘዘው መሠረት፣ እነዚህን ከተሞችና መሰማሪያቸውን ለሌዋውያኑ በዕጣ መደቡላቸው።
9 ከይሁዳና ከስምዖን ነገዶች ደግሞ ከዚህ በታች በስም የተጠቀሱትን ከተሞች በዕጣ መደቡላቸው።
10 እነዚህም ከተሞች የሌዊ ልጆች፣ የቀዓት ጐሣዎች ለሆኑት ለአሮን ዝርያዎች ተመደቡ፤ ይህም የሆነው የመጀመሪያው ዕጣ ለእነርሱ ስለ ወጣላቸው ነበር፤
11 እነርሱም በተራራማው የይሁዳ ምድር ያለችውን ኬብሮን የተባለችውን ቂርያት አርባቅን በዙሪያዋ ካለው መሰማሪያ ጋር ሰጧቸው፤ አርባቅ የዔናቅ አባት ነበረ።