7 ስለዚህ ሙሴ ተመልሶ የሕዝቡን አለቆች አስጠራ፤ እንዲናገር እግዚአብሔር (ያህዌ) ያዘዘውን ቃሎች ሁሉ ነገራቸው።
8 ሕዝቡም ሁሉ በአንድ ላይ “እግዚአብሔር (ያህዌ) ያለውን ሁሉ እናደርጋለን” ብለው መለሱ፤ ስለዚህ ሙሴ እነርሱ ያሉትን መልሶ ወደ እግዚአብሔር (ያህዌ) ወሰደ።
9 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ከአንተ ጋር ስናገር ሕዝቡ እንዲሰሙኝና እምነታቸውን ምንጊዜም በአንተ ላይ እንዲጥሉ በከባድ ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ” ከዚያም ሙሴ ሕዝቡ ያሉትን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) ነገረው።
10 እግዚአብሔርም (ያህዌ) ሙሴን እንዲህ አለው፤ “ወደ ሕዝቡ ሂድና ዛሬና ነገ ቀድሳቸው፤ ልብሳቸውን እንዲያጥቡ አድርግ፤
11 በሦስተኛውም ቀን ይዘጋጁ፤ ምክንያቱም በዚያ ቀን በሕዝቡ ፊት እግዚአብሔር (ያህዌ) በሲና ተራራ ላይ ይወርዳል።
12 በተራራው ዙሪያ ለሕዝቡ ወሰን አበጅተህ እንዲህ በላቸው፤ ‘ወደ ተራራው እንዳትወጡ ወይም ግርጌውን እንዳትነኩ ተጠንቀቁ፤ ማንም ተራራውን ቢነካ በርግጥ ይሞታል።
13 በድንጋይ ይወገራል ወይም በቀስት ይወጋል፤ ምንም እጅ በእርሱ ላይ አያርፍም፤ ሰውም ሆነ እንስሳ በሕይወት እንዲኖር አይተውም።’ ወደ ተራራው መውጣት የሚችሉት ከፍ ባለ ድምፅ መለከት በተነፋ ጊዜ ብቻ ነው።