36 “ከንጹሕ ወርቅ ዝርግ ሳሕን አበጅተህ፣ “ቅዱስ ለእግዚአብሔር (ያህዌ)” በማለት በማኅተም ላይ እንደሚቀረጽ ቅረጸው።
37 ከመጠምጠሚያው ጋር እንዲያያዝ ሰማያዊ ፈትል እሰርበት፤ እርሱም በመጠምጠሚያው ፊት በኩል ይሁን።
38 ይህም በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል፤ እስራኤላውያን ለይተው በሚያቀርቧቸው በማናቸውም የተቀደሱ ስጦታዎች ውስጥ ያለውን በደል ይሸከማል፤ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት ተቀባይነት እንዲኖራቸው ሁል ጊዜ በአሮን ግንባር ላይ ይሆናል።
39 “ሸሚዙን ከቀጭን በፍታ ሥራ፤ መጠምጠሚያውንም ከቀጭን በፍታ አብጀው፤ መታጠቂያውንም ጥልፍ ጠላፊ የሠራው ይሁን።
40 የአሮን ወንድ ልጆች ክብርና ማዕረግ እንዲኖራቸው ሸሚዞችን፣ መታጠቂያዎችን፣ የራስ ማሰሪያዎችን አብጅላቸው።
41 እነዚህን ልብሶች ለአሮንና ለወንድ ልጆቹ ካለበስህ በኋላ ቅባቸው፤ ካናቸው፤ ካህናት ሆነው ያገለግሉኝም ዘንድ ቀድሳቸው።
42 “ከወገብ ጀምሮ እስከ ጭን የሚደርስ ሰውነትን የሚሸፍን ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ቁምጣ አብጅ።