6 መጠምጠሚያውን በራሱ ላይ በማድረግ የተቀደሰውን አክሊል ከመጠምጠሚያው ጋር አያይዘው።
7 ቅብዐ ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ በማፍሰስ ቅባው።
8 ወንዶች ልጆቹን አምጥተህ ሸሚዞች አልብሳቸው።
9 የራስ ማሰሪያዎችንም አድርግላቸው፤ ከዚያም አሮንንና ወንዶች ልጆቹን መታጠቂያዎችን አስታጥቃቸው፤ ክህነት የዘላለም ሥርዐት ይሆንላቸዋል፤ በዚህም መንገድ አሮንንና ወንዶች ልጆቹን ትክናቸዋለህ።
10 “ወይፈኑን በመገናኛው ድንኳን ፊት ለፊት በማምጣት አሮንና ወንዶች ልጆቹ በራሱ ላይ እጆቻቸውን ይጫኑበት።
11 በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ላይ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት እረደው።
12 ከወይፈኑ ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣቶችህ አድርግበት፤ የቀረውንም ከመሠዊያው ሥር አፍሰው።