ዘፀአት 30:12-18 NASV

12 “የእስራኤላውያንን ጠቅላላ ቈጠራ በምታደርግበት ጊዜ እያንዳንዱ ሰው በሚቈጠርበት ወቅት ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆን ወጆ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መክፈል አለበት፤ በዚህም ዐይነት ስትቈጥራቸው በእነርሱ ላይ መቅሠፍት አይመጣም።

13 ማንም ወደ ተቈጠሩት ዘንድ የሚያልፍ ሃያ አቦሊ በሚመዝን በመቅደሱ ሰቅል ሚዛን ግማሽ ሰቅል መስጠት አለበት፤ ይህ ግማሽ ሰቅል ለእግዚአብሔር (ያህዌ) የሚቀርብ መሥዋዕት ነው።

14 ዕድሜያቸው ሃያ ዓመትና ከሃያ በላይ ሆኖ ወደ ተቈጠሩት ያለፉት ሁሉ፣ ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት ማቅረብ አለባቸው።

15 ለሕይወታችሁ ማስተስረያ እንዲሆን ለእግዚአብሔር (ያህዌ) መሥዋዕት በምታቀርቡበት ጊዜ ባለ ጠጋው ከግማሽ ሰቅል በላይ፣ ድኻውም አጉድሎ አይስጥ።

16 የማስተሰረያውን ገንዘብ ከእስራኤላውያን ተቀብለህ ለመገናኛው ድንኳን አገልግሎት አውለው፤ ለሕይወታችሁ ማስተስረያ በማድረግ በእግዚአብሔር (ያህዌ) ፊት የእስራኤላውያን ማስተስረያ ይሆናል።”

17 ከዚያም እግዚአብሔር (ያህዌ) ሙሴን አለው፤

18 “ለመታጠቢያ ከናስ ማስቀመጫው ጋር የናስ ሰን አብጅ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠህ ውሃ አድርግበት።