ዘፍጥረት 22 NASV

አብርሃም ተፈተነ

1 ከዚህ ሁሉ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) አብርሃምን ፈተነው፤ “አብርሃም!” አለው። እርሱም “አቤቱ አለሁ” አለ።

2 እግዚአብሔርም (ኤሎሂም)፣ “የምትወደውን አንዱን ልጅህን፣ ይስሐቅን ይዘህ ወደ ሞሪያ ምድር ሂድ፤ እኔ በማመለክትህ በአንዱ ተራራ ላይ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ሠዋው” አለው።

3 በማግስቱ ጠዋት አብርሃም ማልዶ ተነሣ፤ አህያውን ጭኖ፣ ሁለት አገልጋዮቹንና ልጁን ይስሐቅን ይዞ፣ ለመሥዋዕት የሚበቃውን ዕንጨት ከቈረጠ በኋላ እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳመለከተው ቦታ ለመሄድ ጒዞውን ጀመረ፤

4 በሦስተኛው ቀን አብርሃም ቀና ብሎ ቦታውን ከሩቅ ተመለከተ፤

5 አገልጋዮቹንም “እናንተ አህያውን ይዛችሁ እዚህ ቈዩን፤ እኔና ልጄ ግን ወደዚያ ሄደን ለእግዚአብሔር ሰግደን እንመለሳለን” አላቸው።

6 አብርሃም ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን ዕንጨት ወስዶ፣ ልጁን ይስሐቅን አሸከመው፤ እሳቱንና ቢላዋውንም ራሱ ያዘ። ሁለቱም አብረው ሄዱ።

7 ይስሐቅም አባቱን አብርሃምን፣ “አባቴ ሆይ” አለው።አብርሃምም፣ “እነሆኝ፤ አለሁ ልጄ” አለው።ይስሐቅም፣ “እሳቱና ዕንጨቱ ይኸው፤ ነገር ግን የሚቃጠለው መሥዋዕት የት አለ?” ብሎ ጠየቀ።

8 አብርሃምም፣ “ልጄ ሆይ፤ ለሚቃጠለው መሥዋዕት የሚሆነውን በግእግዚአብሔር ራሱ ያዘጋጃል (ኤሎሂም ይሬህሎ)” አለው። ሁለቱም አብረው ጒዞአቸውን ቀጠሉ።

9 እግዚአብሔር (ኤሎሂም) ወዳመለከተው ቦታ እንደ ደረሱ፣ አብርሃም መሠዊያ ሠራ፤ በላዩም ላይ ዕንጨት ረበረበ፤ ልጁን ይስሐቅንም አስሮ በመሠዊያው ዕንጨት ላይ አጋደመው።

10 ከዚያም ልጁን ለማረድ እጁን ዘርግቶ ቢላዋውን አነሣ።

11 የእግዚአብሔር (ያህዌ) መልአክ ግን ከሰማይ፣ “አብርሃም፤ አብርሃም፤” ብሎ ጠራው፤አብርሃምም፣ “እነሆ፤ አለሁ” አለ።

12 እርሱም፣ “እጅህን በብላቴናው ላይ አታሳርፍ፤ ምንም ጒዳት አታድርስበት፤ እነሆ፤ እግዚአብሔርን (ኤሎሂም) እንደምትፈራ ተረድቻለሁ፤ ልጅህን፣ ያውም አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና” አለው።

13 አብርሃም ቀና ብሎ ሲመለከት በቊጥቋጦ መካከል ቀንዶቹ የተጠላለፉ አንድ አውራ በግ ከበስተ ኋላው አየ፤ ወደዚያው ሄዶ በጉን አመጣና የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ ሠዋው።

14 ከዚህም የተነሣ አብርሃም የዚያን ስፍራ ስም፣ “እግዚአብሔር ያዘጋጃል (ያህዌ ይርኤ)” ብሎ ጠራው፤ እስከ ዛሬም ድረስ፣ “በእግዚአብሔር (ያህዌ) ተራራ ላይ ይዘጋጃል” ይባላል።

15 የእግዚአብሔርም (ያህዌ) መልአክ አብርሃምን ከሰማይ ዳግመኛ ጠራው፤

16 እንዲህም አለው፤ “እግዚአብሔርም (ያህዌ) በራሴ ማልሁ አለ፤ አንዱን ልጅህን ለእኔ ለመስጠት አልሳሳህምና፣

17 በእርግጥ እባርክሃለሁ፤ ዘርህን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር ዳር አሸዋም አበዛዋለሁ። ዘሮችህም የጠላቶቻቸውን ደጆች ይወርሳሉ፤

18 ቃሌን ስለ ሰማህ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።”

19 ከዚያም አብርሃም ወደ አገልጋዮቹ ተመለሰ፤ ተያይዘውም ወደ ቤርሳቤህ ሄዱ፤ አብርሃምም በቤርሳቤህ ኖረ።

የናኮር ልጆች

20 ከዚህ በኋላ እንዲህ ተብሎ ለአብርሃም ተነገረው፤ “ሚልካም ደግሞ የልጆች እናት ሆናለች፤ ለወንድምህም ለናኮር ወንዶች ልጆችን ወልዳለች።

21 እነርሱም የበኵር ልጁ ዑፅና ወንድሙ ቡዝ፣ የአራም አባት ቀሙኤል፣

22 ኮዛት፣ ሐዞ፣ ፊልዳሥ፣ የድላፍና ባቱኤል ናቸው።”

23 ባቱኤልም ርብቃን ወለደ። ሚልካ ለአብርሃም ወንድም ለናኮር የወለደችለት እነዚህ ስምንት ወንዶች ልጆች ናቸው።

24 ከእነዚህም ሌላ የናኮር ቁባት ሬናሕ ደግሞ ጥባሕ፣ ገአም፣ ተሐሽና ሞክሳ የተባሉ ወንዶች ልጆች ወለደችለት።

ምዕራፎች

1 2 3 4 5 6 7 8 9 10 11 12 13 14 15 16 17 18 19 20 21 22 23 24 25 26 27 28 29 30 31 32 33 34 35 36 37 38 39 40 41 42 43 44 45 46 47 48 49 50