18 ንጉሥ ሮብዓም የጒልበት ሠራተኞች አለቃ የነበረውን አዶኒራምን ላከው፤ ነገር ግን እስራኤል ሁሉ በድንጋይ ወግረው ገደሉት። ንጉሡ ሮብዓም ግን እንደምንም ብሎ ሠረገላው ላይ በመውጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሸሸ።
19 ስለዚህ ሕዝቡ በዳዊት ቤት ላይ እስከ ዛሬ ድረስ እንዳመፀ ነው።
20 ኢዮርብዓም መመለሱን እስራኤላውያን ሁሉ በሰሙ ጊዜ፣ ወደ ጉባኤያቸው በማስጠራት በመላው እስራኤል ላይ አነገሡት። ለዳዊት ቤት በታማኝነት ጸንቶ የተገኘው የይሁዳ ቤት ብቻ ነው።
21 ሮብዓም ኢየሩሳሌም በደረሰ ጊዜ፣ የእስራኤልን ቤት ወግተው መንግሥቱን ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም እንዲመልሱ መላውን የይሁዳ ቤትና የብንያምን ነገድ ሰበሰበ፤ የሰራዊቱም ቊጥር አንድ መቶ ሰማንያ ሺህ ነበር።
22 ነገር ግን ይህ የአምላክ ቃል፣ የእግዚአብሔር ሰው ወደ ሆነው ወደ ሳማያ መጣ፤
23 “ለይሁዳ ንጉሥ ለሰሎሞን ልጅ ለሮብዓም፣ ለመላው የይሁዳ ቤትና ለብንያም ነገድ፣ ለቀረውም ሕዝብ ሁሉ እንዲህ በል፤
24 ‘እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ይህ ነገር ከእኔ የሆነ ነውና ወንድሞቻችሁን እስራኤላውያንን ለመውጋት አትውጡ፤ እያንዳንዳችሁ ወደየቤታችሁ ተመለሱ።’ ስለዚህ እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእግዚአብሔርን ቃል ሰሙ፤ ወደየቤታቸውም ተመለሱ።