37 ይህ ሕዝብ፣ አንተ አምላክ እግዚአብሔር እውነተኛ መሆንህንና ልባቸውን የመለስኸው አንተ መሆንህን ያውቁ ዘንድ እባክህ ስማኝ፤ እግዚአብሔር ሆይ፤ እባክህ መልስልኝ።”
38 ከዚያም የእግዚአብሔር እሳት ወርዳ መሥዋዕቱን፣ ዕንጨቱን፣ ድንጋዩንና ዐፈሩን ፈጽማ በላች፤ በጒድጓዱ ውስጥ ያለውንም ውሃ ላሰች።
39 ሕዝቡም ሁሉ ይህን ሲያዩ፣ በግንባራቸው ተደፍተው፣ “አምላክ እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ ነው! እግዚአብሔር እርሱ እውነተኛ አምላክ ነው!” አሉ።
40 ከዚያም ኤልያስ፣ “የበአልን ነቢያት ያዟቸው! አንድም ሰው እንዳያመልጥ” ሲል አዘዘ፤ ሕዝቡም ያዟቸው፤ ኤልያስም ወደ ቂሶን ወንዝ አውርዶ አሳረዳቸው።
41 ኤልያስም አክዓብን፣ “የከባድ ዝናብ ድምፅ ይሰማልና ሂድና ብላ፤ ጠጣም” አለው።
42 ስለዚህ አክዓብ ሊበላና ሊጠጣ ሄደ፤ ኤልያስ ግን ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ጫፍ ወጣ፤ ፊቱንም በጒልበቶቹ መካከል አድርጎ ወደ መሬት አቀረቀረ።
43 አገልጋዩንም፣ “ውጣና ወደ ባሕሩ ተመልከት” አለው።አገልጋዩም ሄዶ ተመለከተና፤ “በዚያ ምንም የለም” አለው።ኤልያስ ሰባት ጊዜ፣ “እንደ ገና ሂድ” አለው።