13 በዚህ ጊዜ የአጊት ልጅ አዶንያስ ወደ ሰሎሞን እናት ወደ ቤርሳቤህ ሄደ፤ ቤርሳቤህም፣ “የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው፤እርሱም፣ “አዎን በሰላም ነው” ብሎ መለሰ።
14 ከዚያም፣ “የምነግርሽ ጒዳይ አለኝ” አላት።እርሷም፣ “እሺ ተናገር” ብላ መለሰች።
15 እርሱም፣ “መንግሥቱ የእኔ እንደ ነበረና እስራኤልም ሁሉ እኔ እንድነግሥ ዐይናቸውን ጥለውብኝ እንደ ነበር አንቺ ራስሽ ታውቂአለሽ፤ ሆኖም ነገሩ ከእግዚአብሔር የተቈረጠለት ሆነና ሁኔታዎች ተለዋውጠው፣ መንግሥቱ ለወንድሜ ተላለፈ።
16 አሁንም አንዲት ነገር እለምንሻለሁ፤ አታሳፍሪኝ” አላት።እርሷም፣ “በል እሺ ተናገር” አለችው።
17 እርሱም፣ “ንጉሥ ሰሎሞን መቼም እምቢ አይልሽምና ሱነማዊቷን አቢሳን እንዲድርልኝ ለምኚልኝ” አላት።
18 ቤርሳቤህም፣ “መልካም ነው፤ ይህንኑ ለንጉሡ እነግርልሃለሁ” ብላ መለሰች።
19 ስለዚህም ቤርሳቤህ የአዶንያስን ጒዳይ ልትነግረው ወደ ንጉሥ ሰሎሞን ሄደች፤ ንጉሡም ሊቀበላት ተነሣ፤ እጅ ከነሣትም በኋላ በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ፤ ንጉሡም ለእናቱ ሌላ ዙፋን አስመጥቶ በቀኙ አስቀመጣት።