20 ቅድስተ ቅዱሳኑም ርዝመቱ ሃያ ክንድ፣ ወርዱ ሃያ ክንድ፣ ቁመቱም ሃያ ክንድ ነበር፤ ውስጡን በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ ከዝግባ የተሠራውንም መሠዊያ በወርቅ ለበጠው።
21 ሰሎሞንም ቤተ መቅደሱን በውስጥ በኩል በንጹሕ ወርቅ ለበጠው፤ በወርቅ በተለበጠው ቅድስተ ቅዱሳን ፊት ለፊትም የወርቅ ሰንሰለቶች ዘረጋ።
22 ስለዚህ ውስጡን በሙሉ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ያለውን መሠዊያም እንደዚሁ በወርቅ ለበጠው።
23 በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው ዐሥር ክንድ የሆነ ሁለት የኪሩቤል ቅርጽ ከወይራ ዕንጨት ሠራ፤
24 የአንደኛው ኪሩብ አንዱ ክንፍ አምስት ክንድ ሲሆን፣ ሌላውም ክንፉ እንደዚሁ አምስት ክንድ ነበር፤ ይህም ከአንዱ ክንፍ ጫፍ እስከ ሌላው ክንፍ ጫፍ ዐሥር ክንድ ማለት ነው።
25 የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ እንደዚሁ ዐሥር ክንድ ሆነ፣ ሁለቱ ኪሩቤል በመጠንና በቅርጽ አንድ ዐይነት ነበሩና።
26 የእያንዳንዱም ኪሩብ ቁመት ዐሥር ክንድ ነበር።