1 ከዚያም ንጉሥ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን የኪዳኑን ታቦት ከዳዊት ከተማ ከጽዮን ለማምጣት፣ የእስራኤልን ሽማግሌዎች፣ የእስራኤልን ነገድ አለቆችና የእስራኤልን ጐሣዎች ሹማምት ሁሉ እርሱ ወዳለበት ወደ ኢየሩሳሌም ጠራቸው።
2 በዓሉ በሚከበርበት ኤታኒም በተባለው በሰባተኛው ወር፣ የእስራኤል ወንዶች ሁሉ ንጉሥ ሰሎሞን ወዳለበት ተሰበሰቡ።
3 የእስራኤል ሽማግሌዎች ሁሉ በመጡ ጊዜም ካህናቱ ታቦቱን አነሡ፤
4 የእግዚአብሔርን ታቦት፣ የመገናኛውን ድንኳንና በውስጡ ያሉትን ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ አመጡ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ይህን ሁሉ ተሸከሙ።