14 ስለዚህ ንዕማን ወረደ፤ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነገረውም በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ትንሽ ልጅ ሥጋ ሆነ፤ ነጻም።
15 ከዚያም ንዕማን ከጭፍሮቹ ሁሉ ጋር ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመልሶ ሄደ፤ በፊቱም ቆሞ፣ “እነሆ በእስራኤል አገር እንጂ በዓለም ሁሉ ሌላ አምላክ አለመኖሩን ተረድቻለሁ፤ ስለዚህ አሁንም ከአገልጋይህ ስጦታ እንድትቀበል እለምንሃለሁ” አለው።
16 ነቢዩም፣ “የማገለግለውን ሕያው እግዚአብሔርን፣ ምንም ነገር አልቀበልም” ሲል መለሰ። ምንም እንኳ ንዕማን አስጨንቆ ቢለምነውም አልተቀበለም።
17 ንዕማንም እንዲህ አለው፤ “ስጦታውን የማትቀበል ከሆነ፣ ለማንኛውም አምላክ የሚቃጠል ወይም ሌላ መሥዋዕት ስለማላቀርብ፣ ሁለት የበቅሎ ጭነት ዐፈር እንድወስድ ትፈቅድልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።
18 ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ አንድ ነገር ብቻ አገልጋይህን ይቅር ይበለው፤ ይኸውም ጌታዬ ለመስገድ ወደ ሬሞን ቤተ ጣዖት በሚገባበት ጊዜ ክንዴን ሲደገፍ እኔም እንደ እርሱ በዚያ ብሰግድ፣ በሬሞን ቤተ ጣዖት በመስገዴ እግዚአብሔር አገልጋይህን ይቅር ይበለው።”
19 ኤልሳዕም፣ “በሰላም ሂድ” አለው። ንዕማን ጥቂት ራቅ ብሎ እንደሄደ፣
20 የእግዚአብሔር ሰው አገልጋይ ግያዝ፣ “ጌታዬ፣ ይህ ሶርያዊ ንዕማን ያመጣውን አለመቀበሉ ደግም አይደል፤ ሕያው እግዚአብሔርን! ተከትዬ ሄጄ ከእርሱ አንድ ነገር ማግኘት አለብኝ” ብሎ አሰበ።