1 ሊቀ ካህናቱም፣ “ይህ የቀረበብህ ክስ እውነት ነውን?” አለው።
2 እስጢፋኖስም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ወንድሞችና አባቶች ሆይ፤ አድምጡኝ! አባታችን አብርሃም ወደ ካራን ከመምጣቱ በፊት፣ ገና በመስጴጦምያ ሳለ፣ የክብር አምላክ ተገልጦለት፤
3 ከአገርህና ከወገንህ ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ሂድ አለው።
4 “እርሱም ከከለዳውያን ምድር ወጥቶ በካራን ተቀመጠ። ከአባቱም ሞት በኋላ፣ አሁን እናንተ ወደምትኖሩበት ወደዚህ አገር አመጣው።
5 በዚህም ስፍራ አንዲት ጫማ ታህል እንኳ ርስት አልሰጠውም፤ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ምንም ልጅ ሳይኖረው፣ እርሱና ከእርሱም በኋላ ዘሩ ምድሪቱን እንደሚወርሱ እግዚአብሔር ቃል ገባለት።
6 ደግሞም እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረው፤ ‘ዘርህ በባዕድ አገር መጻተኛ ይሆናል፤ አራት መቶ ዓመትም በባርነት ቀንበር ሥር ይማቅቃል።
7 ሆኖም በባርነት የሚገዛቸውን ሕዝብ እኔ ደግሞ እቀጣዋለሁ። ከዚያም አገር ወጥተው በዚህች ስፍራ ያመልኩኛል።’
8 ከዚያም የግዝረትን ኪዳን ሰጠው፤ አብርሃምም ይስሐቅን ወለደ፤ በስምንተኛውም ቀን ገረዘው። ይስሐቅም ያዕቆብን ወለደ፤ ያዕቆብም ዐሥራ ሁለቱን የነገድ አባቶች ወለደ።
9 “የነገድ አባቶችም በዮሴፍ ቀንተው በባርነት ወደ ግብፅ ሸጡት፤ እግዚአብሔር ግን ከእርሱ ጋር ስለ ነበር፣
10 ከመከራው ሁሉ አወጣው፤ በግብፅም ንጉሥ በፈርዖን ፊት ሞገስና ጥበብን አጐናጸፈው፤ ፈርዖንም በግብፅና በቤተ መንግሥቱ ሁሉ ላይ ኀላፊ አድርጎ ሾመው።
11 “በዚያ ጊዜም በግብፅና በከነዓን አገር ሁሉ፣ ታላቅ መከራን ያስከተለ ራብ መጣ፤ አባቶቻችንም የሚበሉትን አጡ።
12 ያዕቆብም እህል በግብፅ መኖሩን በሰማ ጊዜ፣ አባቶቻችንን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ግብፅ ላካቸው፤
13 ለሁለተኛ ጊዜ ሲሄዱ ደግሞ ዮሴፍ ማንነቱን ለወንድሞቹ ገለጠ፤ ፈርዖንም ስለ ዮሴፍ ዘመዶች ተረዳ።
14 ከዚህ በኋላ፣ ዮሴፍ ልኮ አባቱን ያዕቆብንና ሰባ አምስት ነፍስ የሚሆኑ ቤተ ዘመዶቹን በሙሉ አስመጣ።
15 ያዕቆብ ወደ ግብፅ ወረደ፤ እርሱም አባቶቻችንም በዚያ ሞቱ።
16 አስከሬናቸውም ወደ ሴኬም ተወስዶ፣ አብርሃም ከዔሞር ልጆች ላይ በጥሬ ብር በገዛው መቃብር ተቀበረ።
17 “እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው ቃል የሚፈጸምበት ጊዜ ሲቃረብም፣ በግብፅ የነበረው የሕዝባችን ቍጥር እየበዛ ሄደ።
18 ከዚያ በኋላ ዮሴፍን የማያውቅ ሌላ ንጉሥ በግብፅ ነገሠ።
19 እርሱም ሕዝባችንን በተንኰሉ አስጨነቀ፤ ገና የተወለዱ ሕፃናታቸውም ይሞቱ ዘንድ ወደ ውጭ አውጥተው እንዲጥሏቸው አስገደዳቸው።
20 “በዚህ ጊዜ ሙሴ ተወለደ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን ያገኘ ውብ ሕፃን ነበር። በአባቱም ቤት ሦስት ወር በእንክ ብካቤ አደገ።
21 ወደ ውጭ በተጣለም ጊዜ የፈርዖን ልጅ አግኝታ ወሰደችው፤ እንደ ራሷ ልጅ አድርጋም አሳደገችው።
22 ሙሴም የግብፆችን ጥበብ ሁሉ ተማረ፤ በንግግሩና በተግባሩም ብርቱ ሆነ።
23 “ሙሴ አርባ ዓመት በሆነው ጊዜ፣ ወንድሞቹን የእስራኤልን ልጆች ሊጐበኝ በልቡ አሰበ።
24 እርሱም፣ አንድ ግብፃዊ ከወገኖቹ አንዱን በደል ሲያደርስበት አይቶ ግብፃዊውንም ገደለ፤ ለተገፋው ወገኑም ተበቀለ።
25 ወገኖቹም እግዚአብሔር በእርሱ እጅ ነጻ እንደሚያወጣቸው የሚያሰተውሉ መስሎት ነበር፤ እነርሱ ግን አላስተዋሉም።
26 በማግስቱም ደግሞ ሁለት እስራኤላውያን ሲጣሉ ደረሰ፤ ሊያስታርቃቸውም ፈልጎ፣ ‘ሰዎች፤ እናንተ እኮ ወንድማማቾች ናችሁ፤ እንዴት እርስ በርሳችሁ ትጐዳዳላችሁ?’ አላቸው።
27 “በባልንጀራው ላይ በደል ሲያደርስ የነበረው ሰው ግን፣ ሙሴን ገፈተረውና እንዲህ አለ፤ ‘አንተን ገና ፈራጅ አድርጎ በእኛ ላይ የሾመህ ማን ነው?
28 ወይስ ትናንት ግብፃዊውን እንደ ገደልኸው እኔንም ልትገድለኝ ትፈልጋልህን?’
29 ሙሴም ይህን እንደ ሰማ ሸሽቶ በምድያም አገር መጻተኛ ሆኖ ተቀመጠ፤ በዚያም ሁለት ወንዶች ልጆች ወለደ።
30 “ከአርባ ዓመት በኋላ፣ በሲና ተራራ አካባቢ ባለው ምድረ በዳ፣ በሚነድ ቍጥቋጦ ነበልባል ውስጥ መልአክ ተገለጠለት።
31 ሙሴም ባየው ነገር ተደነቀ፤ ነገሩን ለማጣራት ወደዚያ ሲቀርብ የጌታ ድምፅ፤
32 ‘እኔ የአባቶችህ አምላክ፣ የአብርሃም፣ የይስሐቅ፣ የያዕቆብ አምላክ ነኝ’ ሲል ሰማ። ሙሴም በፍርሀት ተዋጠ፤ ለመመልከትም አልደፈረም።
33 “ጌታም እንዲህ አለው፤ ‘የእግርህን ጫማ አውልቅ፤ የቆምህባት ስፍራ የተቀደሰች ምድር ናትና።
34 በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በርግጥ አይቻለሁ፤ የጭንቅ ጩኸታቸውን ሰምቻለሁ፤ ላድናቸውም ወርጃለሁ። አሁንም ና፤ ወደ ግብፅ መልሼ እልክሃለሁ።’
35 “እንግዲህ እነዚያ፣ ‘ገዥና ፈራጅ አድርጎ የሾመህ ማን ነው?’ ብለው የናቁትን ይህንን ሙሴ እግዚአብሔር በቊጥቋጦው ውስጥ በታየው መልአክ አማካይነት ገዥና ታዳጊ አድርጎ ወደ እነርሱ ላከው።
36 እርሱም መርቶ ከግብፅ አወጣቸው፤ በግብፅ፣ በቀይ ባሕርና በምድረ በዳ አርባ ዓመት ድንቅ ነገሮችንና ታምራዊ ምልክቶችን አደረገ።
37 “የእስራኤልንም ሕዝብ፣ ‘እግዚአብሔር እንደ እኔ ያለ ነቢይ ከመካከላችሁ ያስነሣላችኋል’ ያላቸው ይኸው ሙሴ ነበር።
38 እርሱም በሲና ተራራ ከተናገረው መልአክና ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ በሕዝቡ ጉባኤ መካከል ነበር፤ የሕይወትንም ቃል ወደ እኛ ለማስተላለፍ ተቀበለ።
39 “አባቶቻችን ግን ተቃወሙት እንጂ ሊታዘዙት ስላልፈለጉ በልባቸው ወደ ግብፅ ተመለሱ።
40 አሮንንም፣ ‘ፊት ፊታችን የሚሄዱ አማልክት አብጅልን፤ ከግብፅ ምድር መርቶ ያወጣን ያ ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅምና’ አሉት።
41 በዚያን ጊዜ የጥጃ ምስል ሠርተው፣ ለጣዖቱ መሥዋዕት አቀረቡ፤ በእጃቸውም ሥራ ተደሰቱ፤ ፈነጠዙም።
42 እግዚአብሔር ግን ከእነርሱ ዘወር አለ፤ ያመልኳቸውም ዘንድ ለሰማይ ከዋክብት አሳልፎ ሰጣቸው፤ ይህም በነቢያት መጽሐፍ እንዲህ ተብሎ በተጻፈው መሠረት ተፈጸመ፤“ ‘እናንት የእስራኤል ቤት ሆይ፤ አርባ ዓመት በምድረ በዳ በነበራችሁ ጊዜ፣መሥዋዕትንና መባን ለእኔ አቀረባችሁልኝን?
43 ይልቁንም ልታመልኳቸው የሠራችኋቸውን፣የሞሎክን ድንኳንና የጣዖታችሁን፣የሬምፉምን ኮከብ ከፍ ከፍ አድርጋችሁ ያዛችሁ።ስለዚህ እኔም እንድትጋዙ አደርጋለሁ፤ ከባቢሎንም ወዲያ እሰዳችኋለሁ።
44 “እግዚአብሔር ለሙሴ ባሳየው ንድፍና ባዘዘው መሠረት የተሠራችው የምስክር ድንኳን፣ ከአባቶቻችን ጋር በምድረ በዳ ነበረች።
45 አባቶቻችንም ድንኳንዋን ከተቀበሉ በኋላ፣ እግዚአብሔር በኢያሱ መሪነት ያሳደዳቸውን የአሕዛብን አገር በወረሱ ጊዜ ይዘዋት ገቡ፤ እስከ ዳዊትም ዘመን ድረስ በምድሪቱ ተቀመጠች፤
46 ዳዊትም በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ በማግኘቱ ለያዕቆብ አምላክ ማደሪያ ያዘጋጅ ዘንድ ለመነ፤
47 ነገር ግን የማደሪያውን ቤት የሠራለት ሰሎሞን ነበር።
48 “ይሁን እንጂ፣ ልዑል የሰው እጅ በሠራው ቤት ውስጥ አይኖርም፤ ይህም ነቢዩ እንዲህ ባለው መሠረት ነው፤
49 “ ‘ሰማይ ዙፋኔ ነው፤ምድርም የእግሬ ማሳረፊያ ናት፤ታዲያ ምን ዐይነት ቤት ትሠሩልኛላችሁ?ይላል ጌታ፤ወይንስ ማረፊያ የሚሆነኝ የትኛው ቦታ ነው?
50 ይህን ሁሉ የሠራው እጄ አይደለምን?’
51 “እናንት ልባችሁና ጆሮአችሁ ያልተገረዘ፣ አንገተ ደንዳኖች ልክ እንደ አባቶቻችሁ መንፈስ ቅዱስን ሁል ጊዜ ትቃወማላችሁ።
52 ከነቢያት መካከል አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን አለ? የጻድቁን መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን እንኳ ገድለዋል፤ እናንተም አሁን አሳልፋችሁ ሰጣችሁት፤ ገደላችሁትም፤
53 በመላእክት አማካይነት የተሰጣችሁንም ሕግ ተቀበላችሁ እንጂ አልጠበቃችሁትም።”
54 በሸንጎው ስብሰባ ላይ የነበሩትም ይህን በሰሙ ጊዜ እጅግ ተጡ፤ ጥርሳቸውንም አፋጩበት።
55 እስጢፋኖስ ግን በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ወደ ሰማይ ትኵር ብሎ ሲመለከት፣ የእግዚአብሔርን ክብር፣ እንዲሁም ኢየሱስ በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አየና፣
56 “እነሆ፤ ሰማያት ተከፍተው፣ የሰው ልጅም በእግዚአብሔር ቀኝ ቆሞ አያለሁ” አለ።
57 በዚህ ጊዜ በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ጆሮአቸውን ደፍነው እርሱ ወደ አለበት በአንድነት ሮጡ፤
58 ይዘውም ከከተማው ውጭ ጣሉት፤ በድንጋይም ይወግሩት ጀመር። ይህ በሚሆንበት ጊዜ በዚያ የነበሩ ምስክሮችም ልብሳቸውን ሳውል በተባለ ጒልማሳ እግር አጠገብ አስቀመጡ።
59 እስጢፋኖስም እየወገሩት ሳለ፣ “ጌታ ኢየሱስ ሆይ፤ ነፍሴን ተቀበላት” ብሎ ጸለየ፤
60 ከዚያም ተንበርክኮ፤ በታላቅ ድምፅ፣ “ጌታ ሆይ! ይህን ኀጢአት አትቍጠርባቸው” ብሎ ጮኸ፤ ይህን ካለ በኋላም አንቀላፋ።